ከሻሸመኔ እስከ ዓለም አቀፍ መድረኮች ቴዎድሮስ ክፍሉ · 2026-11-08
ዩሃንስ ጦና አዲስ አበባ: የኢትዮጵያን ዜማ ከአሜሪካ ጃዝ ጋር ያስማማ ፤ ደግሞም በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ላይ በብዙሃን የተሰማ
ሙዚቃ ድንበር አያውቅም፤ ቋንቋን፣ ብሔርንና የባህል ልዩነትን አልፎ ሰዎችን በአንድ የስሜት ዓለም የሚያገናኝ የጥበብ ቋንቋ ነው። ከአፍሪካ ምድር የተወለዱ የዜማ ስልቶችን ከዘመናዊው የአሜሪካ ጃዝ፣ ጎስፔልና ፈንክ ዜማዎች ጋር በማዋሃድ የራሳቸውን ልዩ የጥበብ ማንነት ከገነቡ ሙዚቀኞች መካከል ዮሐንስ ጦና አንዱ ነው።
ከኢትዮጵያ ሻሸመኔ ተነስቶ በአለም አቀፍ የሙዚቃ መድረኮች ላይ የድምፁንና የጊታሩን ተሰጥኦ ማሳየት የቻለው ይህ ኢትዮጵያዊ አርቲስት፣ የግል ጥረትን፣ የቤተሰብ የሙዚቃ ቅርስን፣ ባህላዊ ትስስርንና የሙዚቃ ትምህርትን በአንድ ላይ ያቀናጀ የሕይወት ታሪክ አለው።
የዮሐንስ ጉዞ የአንድ ሙዚቀኛ የስኬት ታሪክ ብቻ አይደለም፤ ከአንድ የኢትዮጵያ ከተማ የተነሳ የጥበብ ተሰጥኦ በትጋት፣ በትምህርትና በፈጠራ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ትዕይንት ውስጥ እንዴት ሊሳተፍ እንደቻለ የሚያሳይ ድርሳንም እንጂ።
ከሻሸመኔ የተጀመረው የሙዚቃ ፍቅር
ዮሐንስ ጦና በኢትዮጵያ ሻሸመኔ ከሙዚቃ ጋር በተጣመረ ቤተሰብ ውስጥ ተወለደ። ከአዲስ አበባ በግምት 200 ከሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ይህች ከተማ ያሳለፈው የልጅነት ዘመን ለወደፊቱ የሙዚቃ ሕይወቱ መሠረት ሆኗል።
በሙዚቃ የተሞላ የቤተሰብ አካባቢ ውስጥ ማደጉ የሕይወቱን አቅጣጫ ከልጅነቱ ጀምሮ እንዲወስን አግዞታል። አባቱ ኦርጋን የሚጫወት ሙዚቀኛ ሲሆን፣ እናቱ አስቴር ተፈራ በፕሮቴስታንት ዘማሪነቷ የታወቀች ነበረች። ዮሐንስ በኋላም የእናቱን ሦስተኛ አልበም በማዘጋጀት በዝማሬ ሥራዋ ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የሙዚቃ ፍቅሩ የተቀጣጠለው በእናቱ ቤት ውስጥ ከሚደረጉ የመዘምራን ልምምዶች ነበር። የቤተክርስቲያኑ ጊታሪስት በእናቱ ሳሎን ውስጥ ከመዘምራኑ ጋር ሲለማመድ በጥሞና ይመለከት ነበር። የሚሰማውን እያንዳንዱን ኮርድ በልቡ ይይዝና በኋላ በራሱ ለመሞከር ይጥር ነበር።
እናቱ ወደ ሥራ በምትሄድበት ጊዜ ጊታሩን በመያዝ ልምምድ ያደርግ ነበር። ገና የስምንት ዓመት ሕፃን ሳለ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎችን ለእናቱ መጫወት ቻለ። ይህ ድንገተኛ ተሰጥኦ እናቱን አስደንቋት ነበር።
እናቱ ያለ አባት ብቻዋን በአነስተኛ ገቢ ቤተሰቧን ከማስተዳደሯም ባሻገር ፣ የልጇን ተሰጥኦና ፍላጎት በመገንዘብ ሕልሙን እንዲያሳካ የምትችለውን ሁሉ ከፍላለች። የመጀመሪያውን ጊታር ገዝታ ማበርከቷም የሙዚቃ ጉዞውን ወደ ተግባራዊ ሕይወት የቀየረው አስፈላጊ እርምጃ ነበር።
ዮሐንስ የመጀመሪያውን ጊታሩን ሲያስታውስ በፈገግታ ነው። በእርሱ አገላለጽ ጊታሩ ጥራት ያለው አልነበረም፤ በሩሲያ የተሠራ የሚል ፅሁፍ ያለው ቀላል መሣሪያ ነበር። ሆኖም ያ ጊታር ሙዚቃን እንዲማር፣ የሚያገኛቸውን አልበሞችና ቅጂዎችን እንዲያጠና እና የራሱን የጥበብ ቋንቋ እንዲገነባ የመጀመሪያው ትምህርት ቤቱ ሆነለት።
ከሊድ ወደ ቤዝ ጊታር፦ የድፍረትና የፈጠራ ታሪክ
(ሊድ ጊታር: መደበኛ 6 ክሮች (Strings) አሉት። ድምፁ ቀጭን እና ከፍተኛ (High-pitched) ነው።ቤዝ ጊታር ደገሞ ብዙውን ጊዜ 4 ክሮች አሉት ( አልፎ አልፎም ቢሆን የ5 እና 6 ክር ቤዞችም አሉ።) ክሮቹ በጣም ወፋፍራም ሲሆኑ ድምፁ ወፍራም፣ ጥልቅ እና ዝቅተኛ (Low-pitched/Bass) ነው።)
የዮሐንስ የሙዚቃ ጉዞ በሊድ ጊታር መጫወት ብቻ አልተገደበም። በ1995 በሐዋሳ ከተማ ታዋቂው ጀርመናዊ የወንጌል ሰባኪ ራይንሃርድ ቦንኬ በሚሳተፍበት ትልቅ የሃይማኖት ጉባኤ ዋዜማ የቤዝ ጊታር እንዲጫወት ተጠየቀ።
በወቅቱ የቤዝ ጊታር ባለቤት አልነበረም፤ መሣሪያውን መጫወትም አያውቅም ነበር። ይሁን እንጂ በጥቂት ቀናት ውስጥ ዝግጁ እንደሚሆን ለአዘጋጆቹ ቃል ገባ።
ይህንንም ለማሳካት ወደ አንድ አናጺ በመሄድ የስድስት ክር ጊታሩን ወደ አራት ክር ቤዝ ጊታር ለመቀየር ሞከረ። የክሮቹ ብዛት እንዲቀነስና በመሣሪያው አካል ላይ ተገቢው ለውጥ እንዲደረግ አደረገ።
ይህ ውሳኔው በሙዚቃ ችሎታው ብቻ ሳይሆን በድፍረቱና በፈጠራ አስተሳሰቡም ባለ ብሩህ አእምሮ እንደነበር ያረጋግጥልናል። በዚያ የሳምንቱ መጨረሻ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ከምሥራቅ አፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎች ለተሰበሰቡ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተጫወተ። ይህም በአካባቢው የሙዚቃ አድናቂዎች ዘንድ እንዲታወቅ አደረገው።
ይህ ታሪክ ዮሐንስ ከጅምሩ ጀምሮ በችግር ፊት የማይመለስና ያለውን አቅም ተጠቅሞ አዲስ መንገድ ለመፍጠር የሚጥር ሙዚቀኛ መሆኑን ያሳያል።
ከተፈጥሯዊ ተሰጥኦ ወደ ሙያዊ ትምህርት
12ኛ ክፍልን እስኪያጠናቅቅ ድረስ ዮሐንስ በዋነኝነት በራሱ ጥረትና ልምምድ የሙዚቃ እውቀቱን ያዳበረ ነበር። ነገር ግን የጥበብ ተሰጥኦውን በሙያዊ እውቀት ለማጠናከር የተለየ የትምህርት መንገድ መረጠ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በኢትዮጵያ ከሚገኙት የሙዚቃ ትምህርት ተቋማት መካከል ታዋቂ በሆነው እና በጊዜው ብቸኛ በነበረው ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገባ። በዚያም በትምህርቱ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ አሜሪካ ቦስተን ወደ ሚገኘው ታዋቂው በርክሊ የሙዚቃ ኮሌጅ (Berklee College of Music) የሚያስገባ የትምህርት ዕድል አገኘ።
ይህ ዕድል ለዮሐንስ ከአዲስ የሙዚቃ ዓለም ጋር እንዲተዋወቅና የጥበብ አድማሱን እንዲያሰፋ በር ከፈተለት። በተለይም የጃዝ ሙዚቃን፣ የዘመናዊ የሙዚቃ አቀራረቦችንና የተለያዩ የሙዚቃ ዘውጎችን በጥልቀት እንዲያውቅ አስችሎታል።
ከ ኤትዮ የጃዝ ምሽት ወደ አሜሪካ የጃዝ መድረክ
ዮሐንስ ከአሜሪካ ጋር ከመተዋወቁ በፊትም በኢትዮጵያ የሙዚቃ መድረኮች ላይ የተለያዩ ልምዶችን አካብቶ ነበር። በኮፊ ሀውስ እና በታዋቂ የሙዚቃ ማቅረቢያ ቦታዎች ከAfro Sound ባንድ ጋር በመሆን ኤትዮ ጃዝ የሚለውን የሙዚቃ ዘውግ ያቀርብ ነበር።
በዚህ ዘመን ያገኘው ልምድ ባህላዊ የኢትዮጵያ ዜማዎችን ከጃዝ ጋር በማዋሃድ የራሱን የሙዚቃ ማንነት እንዲገነባ አግዞታል። ከቴዲ አፍሮ፣ ዳኒ ወልዴና አዲስ ደመለው ጨምሮ ከተለያዩ ኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ጋር ያደረጋቸው የሙዚቃ ትብብሮችም በዚህ የሙያ ጉዞ ውስጥ ቀድመው ይጠቀሳሉ።
በኋላም ሚኒያፖሊስን በጎበኘበት ወቅት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የሙዚቃ ዳይሬክተር ሆኖ እንዲሠራ ተጋበዘ። ይህ አጋጣሚ በአሜሪካ የጎስፔልና የጃዝ ሙዚቃ ዓለም ውስጥ ለመግባት ወሳኝ መንገድ ከፈተለት።
በሚኒያፖሊስ የሙዚቃ ማኅበረሰብ ውስጥ በአጭር ጊዜ ራሱን ማስተዋወቅ ቻለ። የግራሚ ሽልማት ዕጩ ከነበረው የኤክሰልሲዮር መዘምራን፣ የዶ/ር ማምቦ ጥምረት፣ ዳርኔል ዴቪስ እና የቀረው የወንጌል ቡድን ጋር አብሮ ሠርቷል። እንዲሁም ቲ. ማይቻል ራምቦ፣ ብሩስ ሄንሪ እና ዴቢ ዱንካን ከተባሉ የአካባቢው የሙዚቃ ተወዳጅ ድምፃውያን ጋር ተጫውቷል።
የራሱን የሙዚቃ ማንነት የገለጠበት “Sand from the Desert”
በ1997 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ዮሐንስ በራሱ ሥም የሚጠራውን The Yohannes Tona Band ን መሠረተ። ይህ እርምጃ በራሱ የጥበብ ሐሳብና የሙዚቃ አቀራረብ ላይ የተመሠረተ ሥራ ለመፍጠር ያለውን ፅኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነበር።
በኢትዮጵያ ሚሊኒየም አካባቢ የመጀመሪያውን አልበም “Sand from the Desert” አቀረበ። አልበሙ በሚኒያፖሊስ የጃዝ ማኅበረሰብ ውስጥ የተለየ ትኩረት ያገኘ ሲሆን፣ በዳኮታ ጃዝ ክለብ (Dakota Jazz Club) በተደረገው የሙዚቃ ትርኢት ላይ ባንዱ ከአልበሙ የተወሰኑ ሥራዎችን ለአድማጮች አቀረበ።
የአልበሙ ልዩ መልክ በተለያዩ የሙዚቃ ዘውጎች መካከል ያለውን ድንበር በማስፋት የራሱን የፈጠራ ድምፅ ማቅረቡ ነው። ዮሐንስ የአፍሪካ ዜማዎችን እና የጥንታዊ ሙዚቃ ስልተምቶችን እንዲሁም የዘመናዊ ጃዝ አቀራረቦችን በማዋሃድ “Afrofunkjazz” ብሎ የሚገልጸውን ልዩ የሙዚቃ ቅልቅል ፈጥሯል።
አልበሙ የMiles Davis “Saw What” እና የJohn Coltrane “Naima” ሥራዎችን በAfrofunkjazz አቀራረብ ዳግም የተረጎሙ ቅጂዎችን የያዘ ሲሆን ፤ ከእነዚህ በተጨማሪ አሥር የራሱን የመጀመሪያ የሙዚቃ ድርሰቶች በአልበሙ ውስጥ አካቷል።
“Ride Around Addis Ababa” የተሰኘው ሥራ ከድምፃዊት ሐና ሸንቁጤ ጋር በመተባበር የተሠራ ሲሆን፣ በባህላዊ የኢትዮጵያ የሠርግ ዜማ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ሥራ ዮሐንስ ከልጅነቱ ጀምሮ የተዋወቀውን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ጣዕም ከዘመናዊ የሙዚቃ አቀራረብ ጋር የሚያገናኝ ምሳሌ ነው።
በአልበሙ ላይ ከኒዮ ሶል አቀንቃኟ ድምፃዊት አይሚ ብራያንት ጋር “The Kerims” በተሰኘው ሥራ ላይ በጋራ ተጫውቷል። በተጨማሪም ኪነን ዋናኩ ፣ ዳርኔል ዴቪስ እና ዘ ሪሚናንትስ ጋር የሠራው “World Praize” የተሰኘው የአምልኮ ዝማሬ በምዕራብ አፍሪካዊ የከበሮ ዜማዎች የተቀናጀ ሕያው የሙዚቃ ሥራ ነው።
በአልበሙ ላይ የሚንት ኮንድሽን አባል የሆነው ስቶኪ ዊሊያምስ እና የፒያኖ ተጫዋቹ ናሂቶ ሄሬራን ጨምሮ የተለያዩ ስመ ጥር ሙዚቀኞች ተሳትፈውበታል።
ከሀገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ ሙዚቀኞች ጋር የደመቀው ኮኮብ
የዮሐንስ የሙዚቃ ጉዞ በራሱ ባንድና በሚኒያፖሊስ መድረኮች ብቻ አልተገደበም። ከተለያዩ የሙዚቃ ዘውጎችና ትውልን የመጡ ታዋቂ ሙዚቀኞች ጋር በመሥራት የሙያ አድማሱን አስፋፍቷል።
ከስቶክለይ፣ ዘ ሄድሀንተርስ፣ ዴቭ ኮዝ እና ጀፍሊ ጆንሰን ጋር ያደረጋቸው ጥምረቶች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ካላቸው አርቲስቶችም ጋር አብሮ ሠርቷል።
ከማሕሙድ አህመድ፣ አስቴር አወቀ፣ ጂጂ እና ዓሊ ቢራ ጋር ያለው የሙዚቃ ግንኙነት የኢትዮጵያን የሙዚቃ እሴት ከዓለም አቀፉ የጥበብ መድረክ ጋር ለማዋሀድ ጉልበት ሁኖታል።
በተለይም ከተለያዩ የሙዚቃ ትውልዶች ጋር መሥራቱ የጥበብ አቀራረቡን ሰፊና ተለዋዋጭ እንዲሆን አግዞታል። በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ባህላዊውን የዜማ ቀለም አለመልቀቁ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም ሙዚቃ መልክን በሚገባ ማወቁ ከምርጦቹ ጋር እንዲሰራና ልዩልዩ ፈጠራዎችን እንዲያበረክትልን አስችሎታል ።
ከሻሸመኔ ጠባብ መድረክ እስከ ዓለም ዓቀፍ ታላላቅ ፌቲስቫሎች
በሙዚቃ ሙያው ያስመዘገባቸው ስኬቶች አብረውት ከሰሩት አርቲስቶች ጋር ብቻ አይወሰኑም። በዓለም ዙሪያ ታዋቂ በሆኑ የሙዚቃ መድረኮችና ፌስቲቫሎች ላይ የመሳተፍ ዕድል አግኝቷል።
በለንደኑ Royal Albert Hall፣ በቤልፋስቱ The SSE Arena እና በኒውዮርኩ Carnegie Hall ከThe Gettys ጋር በመሆን በታዋቂ የሙዚቃ መድረኮች ላይ ተሳትፏል።
እንዲሁም በMontreux Jazz Festival፣ North Sea Jazz Festival፣ Red Rocks፣ Hollywood Bowl እና Blue Note የሙዚቃ መድረኮች ላይ ተገኝቷል።
በተለይም ከጃዝ የጋራ ሥራዎቹ መካከል Kenny Garrett እና Joshua Redman ጋር፣ እንዲሁም ከCory Wong ጋር በBlue Note ጋር ያደረጋቸውን የመድረክ ተሳትፎዎች በሙያው ውስጥ የሚጠቀሱ ምዕራፎች ናቸው።
እነዚህ መድረኮች በዓለም የሙዚቃ ባህል ውስጥ ልዩ ቦታ ያላቸው ሲሆን፣ በእነዚህ ቦታዎች መታየት ለአንድ ሙዚቀኛ የሙያ ልምድን ከማስፋት ባሻገር የራሱን የጥበብ ድምፅ ለዓለም አድማጮች የማቅረብ ጥሩ ዕድል እንደሚፈጥሩለት እሙን ነው።
የሙያ እውቅናና ሽልማቶች
ዮሐንስ በሙዚቃ ዘርፍ ባሳየው ተሰጥኦና አስተዋጽኦ የተለያዩ የሙያ እውቅናዎችን አግኝቷል። ከእነዚህ መካከል Minnesota Emerging Composer Award (MECA) ይጠቀሳል። ይህ እውቅና በሙዚቃ ድርሰትና ፈጠራ ዘርፍ ያለውን ችሎታ የሚያመለክት ነው።
“The Jungle Way Out” ከተሰኘው ዘፈን ጋር የGrammy ዕጩነትን አግኝቷል። ይህ በዓለም አቀፍ የሙዚቃ ዘርፍ እጅግ ታዋቂ በሆነው ብዙዎች በሚመኙት ፣ ጥቂቶች በሚታጩበት እና በሚመረጡበት የGrammy ሽልማት ሂደት ውስጥ ያገኘውን እውቅና ያሳያል።
ከዚህም በተጨማሪ በThe Sounds of Blackness አማካኝነት የMid-America Hall of Fame የአባልነት ክብርን አግኝቷል። እነዚህ ስኬቶች በግል የሙዚቃ ሥራው እና ከሌሎች የሙዚቃ ቡድኖች ጋር ባለው ትብብር ያበረከተውን አስተዋጽኦ የሚያሳዩ ናቸው።
የዛሬው ዮሐንስ፦ መነሻውን ያልረሳ የፈጠራ ጉዞ
ዛሬ ዮሐንስ ጦና በራሱ ስም የሚመራውን ባንድ በማስቀጠል በስቱዲዮ የቅጂ ሥራዎችና በቀጥታ የሙዚቃ ትርኢቶች ላይ የጥበብ ድምፁን ማሰማቱን ቀጥሏል። በሥራዎቹ ውስጥ የአፍሪካ ስልተምት እና የአሜሪካ የሙዚቃ ቃና በአንድ ላይ ተዋህደው ይታያሉ።
የሙዚቃ ማንነቱ በአንድ ዘውግ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ዝማሬ ፣ ጃዝ፣ ፈንክ፣ አፍሮ ቢት እና ኒዮ-ሶል እንዲሁም ባህላዊ የኢትዮጵያ ዜማዎች በሥራዎቹ ውስጥ የሚገናኙበት የራሱን ልኬት ፈጥሯል።
ከእናቱ የቀሰመው መንፈሳዊ ዜማ፣ ከልጅነቱ የተዋወቀው የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ፣ በያሬድ የተማረው ሙያዊ እውቀትና በአሜሪካ ያካበተው የጃዝ ልምድ በአንድ ላይ ተጣምረው የራሱን ልዩ የሙዚቃ ዓለም ፈጥረዋል።
ከታወቁት የሙዚቃ ሥራዎቹ መካከል “Sand from the Desert” እና “1317” የተሰኙት አልበሞች ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው በ2000 ዓ.ም አካባቢ፣ ሁለተኛው ደግሞ በ2010 ዓ.ም የተለቀቁ ሥራዎች ናቸው።
በአንድ ጊታር የተጀመረ ታሪክ፣ በዓለም ዓቀፍ እውቅና የቀጠለ ጉዞ
የዮሐንስ ጦና ታሪክ በሙዚቃ ውስጥ ያለው ስኬት በተሰጥኦ ብቻ እንደማይገኝ ያስታውሰናል። የእናት ድጋፍ፣ የልጅነት ሕልም፣ ትጋት፣ ራስን የማሳደግ ፍላጎት፣ የትምህርት ዕድልን መጠቀምና ከተለያዩ ባህሎች መማር በአንድ ላይ ሲጣመሩ ምን ያህል ሰፊ የጥበብ አድማስ ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ያሳያል።
ከሻሸመኔ በእናቱ ቤት ውስጥ የጊታር ዜማዎችን በጥሞና በመከታተል ከልጅነት የተጀመረው ጉዞ፣ ዛሬ በዓለም አቀፍ የሙዚቃ መድረኮች ላይ የሚሰማ የጥበብ ድምፅ ሆኗል።
የዮሐንስ ልዩነት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ መታየቱ ብቻ አይደለም፤ የመጣበትን ባህል ባለመርሳቱ እንዲሁም ከተለያዩ የሙዚቃ ቀለሞች ጋር መስማማቱ እና መዋሃድ መቻሉ ነው።
እሱ ለዓለም የሚያቀርበው ዜማ የኢትዮጵያን አጨዋወት፣ የአፍሪካን ስልተምት፣ የአሜሪካን የጃዝ ባህልና የራሱን የፈጠራ ሐሳብ በአንድ ላይ አዋህዶ የያዘ ልዩ የሙዚቃ ጣዕም ነው።
ዮሐንስ ጦና፤ ከሻሸመኔ የተነሳ፣ የኢትዮጵያን ዜማ ከዓለም የሙዚቃ ቋንቋ ጋር ያገናኘ ድንቅ አርቲስት።
ዩሃንስ ጦና ዩሃንስ ጦና ዩሃንስ ጦና ዩሃንስ ጦና ዩሃንስ ጦና Dagu Ethiopia