በአርሲው የኦርቶዶክሳውያን የጅምላ እልቂት የነማን እጆች በደም ታጥበዋል? ሙሉ ዓለም ገብረመድህን · 2026-11-28
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በአርሲው የኦርቶዶክሳውያን የጅምላ እልቂት ጉዳይ እርምጃ መውሰዱን አምኖ የተገደሉት የትርፍ ጊዜ ተዋጊዎች ናቸው ማለቱን ተከትሎ ጉዳዩ ለፋርሴ ቡላዎችና ለውሃቢያው መንጋም ከፍተኛ የደስታ ምንጭ ሆኖ ሰንብቷል። በቅድሚያም ይህ ታጣቂ ቡድን የዘወትር ምላሽ የፖለቲካ አቀራረብና የመግለጫ ይዘት ወጣ ያለ መሆኑን ይዘን ፣ ማርሸት ጸሃዩ በአርሲ ጉዳይ እንዲናገር የተደረገበትን ቃለ ምልልስ አስታውሰን ፣ እነ አህመድ ዲን ጀቢልና ጀዋር መሃመድ ጉዳዩን በእኩል ስሜት ያጋሩበትን ሁኔታ ጠቅሰን አጠቃላይ ሁኔታዎችን ከታሪክም ካሰላለፍም ከመሰረታዊ ባህሪያት አኳያ እንመረምራቸዋለን።
አንደኛው ጭብጥ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሰባትና ስምንት አመታት በአርሲም ሆነ በወለጋ የሚፈጸሙ የንጹሃን ግድያዎችን በተመለከተ በየጊዜው በሰጣቸው መግለጫዎች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚመራ ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ ለዚህም ፍቃደኛ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጹ ጥሪም ማቅረቡ ይታወሳል። ሁለተኛው ጭብጥ የአርሲው የጥቅምቱ ቀዳሚው የጅምላ እልቂት የተፈጸመው ጥቅምት 14 ቀን ሲሆን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ሪፖርት አደረግኩ ብሎ መግለጫ ያወጣው ጥቅምት 25 ቀን 2019 ዓ.ም ነው። ጥቅምት 26 ቀን ሌላ ዙር የጅምላ እልቂት መፈጸሙን ማስታወስ ይገባል። ታጣቂ ቡድኑ መግለጫ ያወጣው ሰኞ ህዳር ሰባት ቀን 2019 ዓ.ም ነው። ቀዳሚው ጥቃት ከተፈጸመ ከ23 ቀናት በኋላ በእርሱ ላይ መግለጫ ከወጣ ከ12 ቀናት በኋላ መሆኑ ነው። ታጣቂ ቡድኑ በመግለጫው ላይ ባልተለመደ ይዘት በሺርካ ወረዳ እርምጃ መውሰዱን አምኖ የተገደሉት የትርፍ ጊዜ ተዋጊዎች ናቸው ብሏል። የትርፍ ጊዜ ተዋጊ የሚለው አገላለጽ ትርጉሙን ቀድሞ የተጠቀመው የእነ ጀዋር መሃመድ ልሳን የሆነው የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ዶቼ ቬሌ ነው። ሶስተኛው ጭብጥ ከዚህ ቀደም በምስራቅ አርሲ ዞን በኦርቶዶክሳውያን ላይ የጅምላ ጥቃቶች በሚደርሱበት ወቅት መረጃው ለአካባቢው አስተዳደሮች ቀድሞ እንዲደርሳቸው ቢደረግም የቅድመ መከላከል ስራዎችን ከመስራት ይልቅ ስልታዊ ሽፋን በመስጠት የጅምላ ጥቃቱ ስፖንሰር ወይም አጋር መሆናቸውን በተደጋጋሚ አሳይተዋል። ይህ በተጎጂዎችና በዐይን እማኞች አንደበት የተረጋገጠ እውነት ነው። ተጨማሪ ጭብጦችን ማንሳት ቢቻልም ከላይ የጠቀስናቸውን ሶስቱን ጭብጦች ይዘን ወደ ዋናው ጉዳይ እንዘልቃለን።
ከአርሲው የጥቅምቱ የጅምላ እልቂት ጋር ተያይዞ የአሜሪካ መንግስትን ጨምሮ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት የክርስቲያኖች ጥቃት ዓለም አቀፋዊ ስጋት አድርገው በመረዳት ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው በወኪሎቻቸው በኩል ገልጸዋል። በርካታ ሚዲያዎች በጉዳዩ ላይ ሰፊ የዘገባ ሽፋን ሰጥተዋል። ይህ ሁኔታ በኦህዴድ ብልጽግና መንደር ከፍተኛ መደናገጥን ፈጥሯል። የአክራሪነት አስተምህሮቱን ሲረጭ በከረመው ሃይል ላይም እንደዚሁ። አጀንዳውን ለማጥፋት እንደ ጀዋር መሃመድ ያሉ የውጭ ክንፎች የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ዶቼ ቬሌ ላይ ቀርበው በአርሲ መንግስት ግለሰቦችን የማስታጠቅ ስራ በመስራቱ ነው ይህ የእርስ በርስ ግጭት የተቀሰቀሰው ሲል የትርክት ቅልበሳ ፣ የወንጀል አጠባ ለማድረግ ሞክሯል። ከዚህ የጅምላ ጥቃት ከ23 ቀናት በኋላ ባልተለመደ የመግለጫ ይዘት አቀራረብ የመጣው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦላ) እርምጃ የወሰደባቸው ፓርት ታይም ኮምባታንትስ እንደሆኑ ገለጸ። የሴራው ቋጥሮ ያለው እዚህ ላይ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ በነበሩ መግለጫዎች እንደ ድርጅት አቋሙን ሲገልጽ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚመራ ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ ለዚህም ፍቃደኛነቱን ደጋግሞ ገልጾ ነበረ። አሁን 180 ዲግሪ ታጥፎ እርምጃ መውሰዱን አምኖ ነገር ግን እርምጃው የተወሰደው በሚል ለንጹሃን ማቾች የሰጠው ሚና ቀደም ሲል እነ ጀዋር መሃመድ ከሚጠቀሙበት የትርክት ቅልበሳና የወንጀል አጠባ ጋር የሚዛመደውን በግል የታጠቁ የሚል ነው። እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመዋቅር ደረጃ መረጃዎችን አጣርታ ይፋ ባደረገችው የሟቾች ስም ዝርዝር ውስጥ የአራትና የአምስት አመት ህጻናት ፣ አዛውንቶች እና እመጫቶች እንደሚገኙበት ማስታወስ ይገባል። በነ ጃል ጅሬኛ እና ጀዋር መሃመድ ብያኔ እነዚህ ነፍስ ያላወቁ ህጻናትና እመጫቶች አልጋ የያዙ አዛውንቶችና አሮጊቶች የትርፍ ጊዜ ታጣቂዎች ናቸው ማለት ነው? በርግጥ እውነታው ወዲህ ነው። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ትብብር በተባለው የሰባት ታጣቂዎች ጥምር ጉዳይ የውስጥ ልዩነቶች አሉ። ከጀምሩም የዳር እንጂ የማሀል ተዋናይ አልነበረም። በአመራር ውስጥ የፖለቲካ ሃይሎች አሰላለፍ ትንተና ልዩነት አጋጥሟል። በተለይም ኦህዴዶች ዘንድ ወለጋ ላይ እራስን በመከላከል ምርህ ከአማራ ፋኖ ሃይል የገጠማቸው ምት ቅስማቸውን የሰበረ መሆኑን ተከትሎ የገዢው መደብ ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ ነው። እናም ለታጣቂ ቡድኑ አመራሮች ቢያንስ በከፊል በከፍተኛ ገንዘብ እና በገዳ ሽምግልና ድለላ በጥቅም የተገዙ ሰዎች መግለጫ እንዲወጣ በማድረግ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን አዲስ የወዝግብ አጀንዳ በመክፈት ፋርሴ ቡላዎችንና የአህመድ ዲን ጀበልን መንጋ በጋራ አስጨፍረውታል።
በኦሮሞ ሃይሎች ዘንድ በተለይም እንደ አሜባ እየተበጣጠሰ በመጣው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ውስጥ የትጥቅ ትግል መሰረቶች ሁለት ጽንፎች አሉ። የምዕራብና የምስራቅ ጽንፎች። የምዕራቡ ክፍል የወለጋው ሃይል ሲሆን እስከ ሸዋ ያለውን ሃይል የማቀፍ ተሞክሮ አለው። የምስራቁ ክንፍ ዋና መሰረቱ ሀረርጌ ሆኖ ባሌና አርሲ ዋና መሰረቱ ናቸው። ይህ የምዕራብና የምስራቅ ክንፍ የትግል ትንተናውም ሆነ የትግል አተያዩ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ በተቃርኖ የተሞሉ ልዩነቶች አሉበት። መሰረታዊ ልዩነቱ ከሃይማኖትና ከባህል ጋር ይያያዛል። የዚህ አተያይ ልዩነት ውጤት የሆኑት ባሮ ቱምሳና ጃራ አባ ገዳ ታሪካቸው የሟችና ገዳይ ሆኖ እንደ ገንዱማ ዛሬም የትርክት እዳ ሆኖ ዘልቋል።
የወለጋው ሃይል ምዕራቡ ክፍል ኢምፓየር ሲል የሚጠራትን ኢትዮጵያንና ሀገረ መንግስቷን ለመናድ የአቢሲኒያ ጭንቅላቶችን መምታት የሚል የጸና አቋም ሲኖረው ዓለም አቀፍ አጋርነቱም ፕሮቴስታንታዊ ማህበራዊ መሰረት ባላቸው እንደ ጀርመንና ኖርዌይ ባሉ የምዕራብ ሀገራት ላይ አድርጓል። በጸረ ደርግ ትግል ወቅት ከሱዳንም ከወያኔም ከሻዕቢያም የፈጠራቸው ጥምረቶች ሁሉ መሰረታዊ አላማውን እንዲጋፉበት አይፈቀደም ነበረ። በአንጻሩ የሀረርጌው አርሲና ፣ የባሌው እስላም የምስራቁ ክፍል ኢትዮጵያ ማለት የደገኛ ክርስቲያን "አማራ ማለት" ክርስቲያን ማለት ነው። ዛሬም ድረስ በአርሲ ባሌና ሀረርጌ አማራ ነኝ ማለት ክርስቲያን እንደማለት የሚቆጥሩ የብሉይ ዘመን ሰዎች አሉ። እናም የጃራ ቡድን ገና ከዘመነ ደርግ ጀምሮ የትግል ግምገማው ከክርስቲያን ገዢዎች ነጻ መውጣት እስላማዊ ኦሮሚያን መፍጠር ለዚህ ግቡ ማሳኪያ ደግሞ ከሳውዲ አረቢያ እስከ ዝያድ ባሬ ድረስ እርዳታ ፍለጋ በርካታ ልዑኮችን እንደላከ ሊንጮ ለታ ትግል ህይወቱ በተሰኘው የኑዛዜ ድርሳኑ ላይ ሳይሸሽግ ነግሮናል። ይህ ታሪካዊ መሰረት ያለው ልዩነት በራሱ በኦህዴድ ብልጽግና መዋቅር ውስጥ ጭምር የትግል ትንተና ተጽዕኖ ያመጣ መሆኑ ይነገራል። የሆነ ሆኖ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ሃይል በአሁኑ ሰዓት በአንድ ወጥ የዕዝ ተዋረድ የሚያዘው ሃይል አለው ከተባለ የምዕራቡ ክፍል እንጂ የምስራቁ ክፍል የቀደመ የልዩነት መስመሩን ጠብቆ በራሱ የአመጽ መንገድ የተሰማራ ሃይል ነው። ከነ ጃል ማሮ ቡድን ጋር በአንድ ቋንቋ ከመነጋገራቸውና የጋራ ጠላት አማራ ኦርቶዶክስ ከመፍጠራቸው ውጪ ይህ ነው የሚባል ሀገራዊ ቀጠናዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ የጋራ ትግል ምልከታ የላቸውም።
የምስራቁ ክፍል ታጣቂ ሃይል ከዚያው ከአካባቢው አስተዳደር በዲን በሃይማኖት ስም ከመቀራረብ ጀምሮ የግንኙነት ሰንሰለቱ ከሞቃዲሾ እስከ ታችኛው ሸበሌ ተፋሰስ ድረስ የተዘረጋ ነው። ከአይኤስኤስና ከአልሸባብ ተከታታይ ዙር ስልጠናዎችን ይወስዳል። ይህ ሃይል ከአክራሪነት አስተምህሮቱ በመነሳት በአርሲ ተደጋጋሚ የጅምላ እልቂቶችን ይፈጽማል። የአመለካከቱ ደጋፊ የሆኑ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት የተቀናጀና ስልታዊ ድጋፍ ያደርጉለታል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአካባቢው በስም የተለዩ ሶስት ዋና ዋና ብርጌዶች አሉ። እነዚህ አባሎቻቸው በሶማሊያ በሚገኙ የአልሸባብ ካምፖች አክራሪ የኢንዶክትሪኔሽን ትምህርትና የሽብር ስልጠና ወስደው ወደ ቀጠናው የገቡ ናቸው። እነዚህ ሃይሎች የሃይማኖት አክራሪነት እንቅስቃሴያቸውን ለመሸፈን የኦነግ ዩኒፎርም የትግል አላማና የጸጉር አሰራር ስታይል ይጠቀማሉ። በዚህ ጉዳይ መረጃዎችን ስከታተል የተሻለ የመረጃ ምንጭ ሆን ያገኘሁት የኢትዮ ፎከስ ዘገባ ነው። አንደኛ ነዲ ገመዳ ብርጌድ ከሽርካ ሆንቆሎ ዋቤ ገደብ አሳሳ እስከ ሻሸመኔና ምስራቅ ሸዋ ድረስ በመሻገር የሚንቀሳቀስ። ሁለተኛው መዳ ወላቡ ብርጌድ የሸርካ ሮቤ ጢቾ አሚኛ ሴሩና አጎራባች ወረዳዎችን የሚሸፍን። ሶስተኛው ሃምባ አኖሌ ብርጌድ ጉና ምርቲ ጀጁ አስኮ ጮሌና ጎሎልቻ ወረዳዎችን ያቀፈ ነው። እነዚህ አክራሪ ጽንፈኛ ሃይሎች ዋና የመውጫና የኢንዶክትሪኔሽን ኮሪደራቸው በሶማሌ ክልል ውስጥ ወደ ሞቃዲሾ የሚያስኬደው መንገድ እንደሆነ እስከ ሞቃዲሾ ድረስ በመሄድ በታችኛው ሸበሌ ከአልሸባብና ከተለያዩ አካላት ጋር ወታደራዊ ስልጠና እንደሚወስዱ ለእስላማዊ መንግስት ምስረታ አላማ የርዕዮተ ዓለም ስልጠና እንደሚያገኙ የክትትል መረጃዎች ያሳያሉ። በተጨማሪም እነዚህ ሃይሎች በሻሸመኔ አሰላና ባሌ ከሚገኙ የከተማ መዋቅሮች እንዲሁም ከአካባቢው የመንግስት መዋቅር ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። የክትትል መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በምስራቁ ክፍል ያለው የዚሁ አክራሪ ሃይል አሁናዊ እንቅስቃሴና የእድገት ደረጃ ቀጠናውን ወደ አልሸባብ የስምሪት ማዕከልነት ሊቀይረው ይችላል። በተጨባጭ አርሲ ባሌና ሀረርጌ ከፍተኛ የሽብርተኝነት ስጋት አለ። በእነዚህ አካባቢዎች ከቀበሌ እስከ ዞን አስተዳዳሪዎች ድረስ ያሉ አመራሮች የዚህ አስተሳሰብ ተጠቂ ናቸው። ዋነኞቹ የኦህዴድ ብልጽግና ገዢዎች ይህን አደገኛና ውስብስብ የሽብር መረብ በሚገባ ያውቁታል።
ችግሩ ሁለት ነው። አንድም በቀውስ ውስጥ አላማን ለማሳካት ሽብር እንደ አመራር ዘይቤ በፍኖተ ካርታ ደረጃ እንደ ፕሮጀክት የተያዘ መሆኑ ፤ ሁለተኛው ጉዳይ ግን የታሪክ መሰረት ያለው የምዕራብና ምስራቅ ጎራ ጽንፍ በኦህዴድ ብልጽግና አቅም የሚታረቅ ባለመሆኑ በወለጋም አማራውን ማጽዳት በአርሲም ኦርቶዶክሱን ማጥፋት በጋራ የሚያቆም የጥላቻ መግባቢያ ቋንቋቸው መሆኑ ጋር ይያያዛል። እዚህ ላይ ነው ጃል ጅሬኛንም ጀዋር መሃመድንም አህመዲን ጀበልንም እኩል ተሰልፈው የምናገኛቸው። ከፊሉን የአክራሪነት አስተምህሮ ቀሪውን ደግሞ ከደም ቁማር የሚገኝ ጥቅም አዛምዶታል። ሃቂቃው ይኸው ነው።
ሙሉ ዓለም ገብረመድን
የአርትዖት ማስታወሻ
ይህ ጽሑፍ የጸሐፊውን የግል አመለካከት፣ ትንታኔና ነፃ አስተያየት የሚያንጸባርቅ ሲሆን፣ የዳጉ ኢትዮጵያ ሚዲያን ኦፊሴላዊ አቋም ወይም አስተያየት የግድ አይወክልም። በጽሑፉ ውስጥ የተነሱ አመለካከቶች፣ ትንታኔዎችና ክሶች የጸሐፊው ኃላፊነት ሲሆኑ፣ አንባቢዎች ይዘቱን በጥንቃቄ እንዲመዝኑና ከሌሎች ምንጮች ጋር እንዲያነጻጽሩ ይመከራል። ዳጉ ኢትዮጵያ የተለያዩ አመለካከቶችንና የአስተያየት ነፃነትን ያከብራል።
Dagu Ethiopia