አስከፊው ጦርነት ከደጅ ቁሟል ፤ ዮሴፍ ምህረቱ · 2026-11-14
አዲስ አበባ: የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ብልሽት እየተባባሰ መምጣቱ በአፍሪካ ቀንድ አዲስ የመንግሥታት ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለውን ስጋት አንሮታል። ዓለም አቀፉ የቀውስ ቡድን (International Crisis Group) በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ውጥረት “በቀላሉ ሊጀመር የሚችል፣ ለማቆም ግን አስቸጋሪ የሚሆን ጦርነት” ሲል ገልጾታል።
ከ1990 እስከ 1992 ዓ.ም በሁለቱ አገራት መካከል የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ከተቋጨ ሩብ ምዕተ ዓመት ቢቆጠርም ፣ ተመሳሳይ ታሪክ እንዳይደገም ስጋትን ፈጥሯል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የድንበር ከተማ በሆነችው በባድመ እና በዙሪያዋ የሚደረጉ መጠነኛ ውጊያዎች ለአካባቢው ነዋሪዎች የመፈናቀል ምክንያት ለተቀረው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ የስጋት ዋነኛ ምንጭ ሆኗል።
የአስመራ እና የአዲስ አበባ ተደጋጋሚ የተቃርኖ ክሶች
ውዝግቡ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደረጃ በደብዳቤ ልውውጥም ቀጥሏል። ኢትዮጵያ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ለምክር ቤቱ በላከችው ደብዳቤ፣ የኤርትራ ጦር “ሙሉ ወረራ” እንደፈፀመባት ገልጻ፣ ራሷን ከመከላከል ውጭ አማራጭ እንደሌላት ጠቅሳለች። አዲስ አበባ የኤርትራ ጦር እስከ 60 ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ ትግራይ ግዛት ገብቷልም ብላለች።
አስመራ ግን ይህንን ክስ አጣጥላለች። የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳላሕ፣ የወረራ ክሱ ኢትዮጵያ የጦርነት ሰበብ ለመፍጠር የምታደርገው ሙከራ ነውም ብለዋል። እንዲሁም የኢትዮጵያን ክስ ጦርነት ማወጅ እንደሆነ በመግለጽ፣ የጸጥታው ምክር ቤት አግባብ ያለውን የመከላከያ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቃለች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በበኩላቸው፣ በተመድ ቻርተር አንቀጽ 51 ሥር የተደነገገውን ራስን የመከላከል መብት ቢጠቅሱም መንግሥታቸው ምን ዓይነት እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ግን በዝርዝር አልገለጹም።
በዚህ ሁኔታ ሁለቱም መንግሥታት ራሳቸውን የጥቃት ሰለባ አድርገው እያቀረቡ ሲሆን፣ ይህም ወደ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለመመለስ የበለጠ አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችል ተንታኞች ያስጠነቅቃሉ።
በሁለቱም በኩል ያለው ወታደራዊ ሀይል
የቱርኩ የዜና ድርጅት አናዶሉ፣ የኢትዮጵያ ጦር ታንኮችንና ከባድ መሣሪያዎችን ወደ ኤርትራ ድንበር እያንቀሳቀሰ መሆኑን ዘግቧል።
በአሜሪካ የሚገኘው የግጭት ክስተቶችን የሚከታተለው ACLED በበኩሉ፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች ባገኘው መረጃ መሠረት ብዙ ታንኮችና ከባድ መሣሪያዎች ከአዲግራት ተነስተው ወደ ፋጺና ዛላምበሳ አቅጣጫ ሲያልፉ እንደታዩ ገልጿል። ድርጅቱ በአካባቢው የሚገኙ የኤርትራ ጦር ክፍሎች ወደ ደብረ ዳሞና ኢሮብ አቅጣጫ ወደ ኋላ የሚመለሱ ይመስላልም ብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ከህዳር 1 ጀምሮ ተከታታይ መጠነኛ ወጊያዎች በኢትዮጵያና በኤርትራ ወታደሮች መካከል እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሷል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም በኢትዮጵያ ላሉ አሜሪካውያን የረጅም ርቀት ሚሳይል ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል የሚያስገነዝብ የአደጋ ማስጠንቀቂያ እንደሰጠ ፎክስ ኒውስ ዘግቧል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ቶሚ ፒጎት፣ በሁለቱ አገራት መካከል የሚነሳ ጦርነት በመላው ቀጣናው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በመግለጽ፣ ሁለቱም ወደ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እና መዘዞቹ
ለሦስት አስርተ ዓመታት የኢትዮጵያንና የኤርትራን ፖለቲካ የተከታተሉት ብሪታኒያዊው ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውት፣ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ብትፈጽም እንደሚታሰበው ፈጣንና ቀላል ዘመቻ እንደማይሆን ያስጠነቅቃሉ።
ፕላውት አዲስ አበባ ሊያጋጥሟት ይችላሉ ብሎ ከጠቀሳቸው አምስት ዋና ዋና አደጋዎች መካከል። የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ሕጋዊነት ነው። ኤርትራ በተመድ እውቅና ያገኘች ሉዓላዊ ሀገር በመሆኗ፣ በላይዋ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸም ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፍ ውግዘት ሊያጋልጣት እንደሚችል ይገልጻሉ።
ሁለተኛው የወታደራዊ አቅርቦትና ሎጂስቲክስ ችግር ነው። የኢትዮጵያ ጦር ወደ ኤርትራ ውስጥ በገፋ ቁጥር የአቅርቦት መስመሮቹ ሊረዝሙና ለጥቃት ተጋላጭ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ያስረዳሉ።
ሦስተኛው የትግራይ ጉዳይ ነው። የትግራይ መከላከያ ኃይሎች ከመቐለ ወደ ተራራማ አካባቢዎች መመለሳቸውን የጠቀሱት ፕላውት፣ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ኤርትራ ከገፋ ከኋላው በጉሬላ ውጊያ ሊያጠቁት እንደሚችሉ ይናገራሉ።
አራተኛው ጥቃት በኤርትራ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት ተቃዋሚዎችን በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዙሪያ ሊያሰባስብ መቻሉ ነው። አምስተኛው ደግሞ ከውጭ አገራት የሚመጣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጫና ነው። ፕላውት ኤርትራ ከግብፅና ሱዳን ጋር ያላትን የቆዬ ወዳጅነት እንዲሁም ከአሜሪካ ጋር የጀመረችውን የታደሰ እና የተሻሻለ የግንኙነትን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ የሚመጣውን ጫና መቋቋም ሊከብዳት እንደሚችል ይገምታሉ።
የባሕር ኃይል አዛዡ ማስጠንቀቂያ
ከቀን ወደ ቀን እየጠነከረ የመጣው የአዲስ አበባው ፖለቲካዊ ፍላጎት በአመራሮቹ የአደባባይ ንግግሮች ላይ በግልፅ ይንፀባረቃል ፤ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ከአራት ቀናት በፊት ህዳር 1,2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደ አንድ የውይይት መድረክ ላይ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትን ከተቻለ በዲፕሎማሲያዊና በሕጋዊ መንገዶች እንደምታስመልስ፣ ሆኖም ይህ ሳይሳካ ቢቀር የሀይል አማራጭን እንደምትጠቀም ገልፀው ፣ አድሚራሉ አሰብና ምጽዋን በሥም ጠቅሰው፣ ወደቦቹ ታሪካዊ ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
የባሕር በር ፍላጎትና የጦርነት ፈተና
ፕላውት ኢትዮጵያ ኤርትራ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ልትፈጽም የምትችልባቸውን ገፊ ምክንያቶችምን የጠቀሱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛው በቀይ ባሕር ላይ ቀጥተኛ የባለቤትነት ድርሻ ማግኘት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተደጋጋሚ እንዳሉት የዐሰብ እና የማሳዋ ጉዳይ ከወደብ በላይ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህም ባሻገር የ አራት ኪሎው መንግስት ኤርትራን በወዳጅ መንግሥት መተካት ወይም አገሪቱን በሌላ መንገድ መቆጣጠር የሚል ሐሳብ ሊኖር እንደሚችል ፕላውት አልሸሸጉም ።
በወታደራዊ አቅም ረገድ፣ ፕላውት የኤርትራ ጦር ቁጥር 350 ሺህ ያህል እንደሆነ ቢገምቱም፣ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እጥረት እንዳለበት ይገልጻሉ። ኤርትራ ወደ ሰባት የሚጠጉ በሥራ ላይ ያሉ የጦር አውሮፕላኖች ቢኖሯትም የሚሠሩ የውጊያ ጄቶች ግን እንደሌሏት ጠቅሰዋል። እነዚህ ቁጥሮች ግን በገለልተኛ መረጃ የተረጋገጡ አይደሉም።
የቀጣናው ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታ
የቀድሞው የሲአይኤና የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ካሜሮን ሁድሰን፣ የአሜሪካ መንግሥት በጉዳዩ ላይ የበለጠ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ሁድሰን የኤርትራ ጦር ወደ ኢትዮጵያ እየገባ እንደሆነና በኢትዮጵያ ያሉ መንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖች መንግሥትን ለመጣል በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ግብፅ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኤርትራ ያወጡትን የጋራ መግለጫ፣ በቀይ ባሕር የሁቲዎች እንቅስቃሴና ከኢራን ጋር የተያያዘውን ግጭትም የቀጣናውን ሁኔታ የበለጠ የሚያወሳስቡ ጉዳዮች እንደሆኑ አስታውሰዋል።
የግንኙነቱ ታሪካዊ ዳራ
ኤርትራ በ1986 ዓ.ም ነፃነቷን ካገኘች በኋላ፣ በ1990 በሁለቱ አገራት መካከል የድንበር ጦርነት ተነስቶ እስከ 1992 ቀጥሏል። በ2010 ዓ.ም የሰላም ስምምነት በመፈረሙ ግንኙነታቸው የተሻሻለ ቢመስልም ከ2013 እስከ 2014 በትግራይ በተካሄደው ጦርነት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ተሰልፎ ተዋግቷል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት የሚቀርበው ሙግት ፣ በኤርትራ በኩል የወደብ ሉዓላዊነትን ለመጋፋት የተደረገ አደገኛ ሙከራ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፣ በተለይም የዓሰብ ጉዳይ የውዝግቡ ዋና ማጠንጠኛ ሆኗል።
ዓለም አቀፍ ምላሽ
በፓሪስ ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 1 ቀን 2019 ዓ.ም. በተካሄደው የG7 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ውጥረት በዲፕሎማሲያዊ ደረጃ ተነስቷል። ሚኒስትሮቹ ሁለቱም አገራት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ የሌላውን አገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲያከብሩ እና ለሰብዓዊ ዕርዳታ መዳረሻ እንዲፈቅዱ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም የተመድና የአፍሪካ ሕብረት የሚያደርጉትን የሽምግልና ጥረት ደግፈዋል።
ሆኖም መግለጫው የቅጣት እርምጃም ሆነ የተወሰነ የጊዜ ገደብ አልያዘም። ይህም የመፍትሔ ፍለጋውን በዋናነት በክልላዊ ድርጅቶች የዲፕሎማሲ ጥረት ላይ የሚተው ሆኗል።
ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች
በቀጣይ ሳምንታት የሚታዩ አንዳንድ ክስተቶች ሁኔታው ወዴት እንደሚያመራ በግልፅ ሊያመለክቱ ይችላሉ።
የመጀመሪያው በአናዶሉና ACLED የተዘገቡት የጦር ሰራዊት እንቅስቃሴዎች ይቀጥላሉ ወይስ ይረግባሉ?
ሁለተኛው ተ.መ.ድ ወይም የአፍሪካ ሕብረት ወደ ሁለቱም ዋና ከተሞች በመሄድ ተዓማኒ የሽምግልና ሂደት ያስጀምር ይሆን ወይ?
ሦስተኛው የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ወደ ግጭቱ መግባታቸው ሲሆን፣ ይህ ከድንበር ውጥረት ወደ ብዙ ግንባር ጦርነት ሊቀይረው ይችላል።
አራተኛው የባሕረ ሰላጤው፣ የግብፅና የአሜሪካ መንግሥታት ሁለቱን ወገኖች ወደ መረጋጋት ለመመለስ የሚያደርጉት ጫና ወይም የሚይዙት አቋም ነው።
ተንታኞች የሚያነሱት ዋነኛ ማስጠንቀቂያ፣ ፈጣንና ውጤታማ የዲፕሎማሲ ጥረት ካልተደረገ የቀጣናው ሕዝብ ወደ ከፋ ቀውስ ሊገባ እንደሚችል ነው። ነገር ግን ከሁለቱም ወገኖች የሚወጡ ክሶች፣ ከጦር ሠራዊት ብዛት እስከ ድንበር ጥሰት ድረስ ያሉ ብዙዎቹ መረጃዎች አሁንም አከራካሪና በገለልተኛ አካል ያልተረጋገጡ ቢሆኑም የአደጋው አፍጦ መቅረብ ግን አያጠያይቅም።
Dagu Ethiopia