በኢትዮጵያ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር ወደ 790 አደገ፤ የባለሙያ ፍልሰትና የሕክምና መሣሪያዎች እጥረት አሳሳቢ ሁኗዋል ትህትና ሲሳይ · 2026-11-21
አዲስ አበባ- በኢትዮጵያ በመኪና አደጋ፣ በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ በሚደርሱ ጉዳቶችና በጦርነት እንዲሁም በግጭቶች ምክንያት የሚከሰቱ የአጥንት ስብራቶች ለአጥንት ቀዶ ሕክምና ፍላጎት ከሚያሳድጉ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል መሆናቸው ተገለጸ። ከ132 ሚሊዮን በላይ እንደሚገመት ከተገለጸው የሀገሪቱ ሕዝብ ብዛት አንጻር የአጥንት ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር አሁንም በቂ እንዳልሆነ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ማኅበር 19ኛውን ዓመታዊ ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ ከአሥር ዓመት በፊት ከ40 ያልበለጠው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ቁጥር አሁን በሥልጠና ላይ ያሉትንና ተባባሪ አባላትን ጨምሮ ወደ 790 አድጓል። ይህ በዘርፉ የሰው ኃይል ለማሳደግ የተደረገውን ጥረት ቢያመለክትም፣ ከሀገሪቱ የሕክምና ፍላጎት አንጻር የባለሙያዎች እጥረት አሁንም እንደቀጠለ ተጠቁሟል።
ጉባኤው በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት “የአጥንት ቀዶ ሕክምናን ማዘመን፡ ከሳይንሳዊ ትንታኔ ወደ ማኅበረሰብ የትብብር ተጽዕኖ” በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደ ሲሆን፣ በሀገሪቱ የአጥንት ጉዳቶች ዓይነትና መንስኤዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
በጉባኤው ላይ በአዋቂዎች የታችኛው የሰውነት ክፍል፣ በተለይም በእግር አካባቢ የሚደርሱ ጉዳቶች በብዛት እንደሚታዩ ተገልጿል። በላይኛው የሰውነት ክፍል ደግሞ የእጅ ጉዳቶች የተለመዱ ሲሆኑ፣ በሕፃናት ላይ ከመውደቅ ጋር የተያያዙ ጉዳቶች በብዛት እንደሚከሰቱ ተመልክቷል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤፍሬም ገብረሃና እንደገለጹት፣ ማኅበሩ በአስር ዓመታት ውስጥ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስቶችን የሚያሰለጥኑ ተቋማትን ከአንድ ወደ 13 ማሳደግ ችሏል። በዘንድሮው ዓመትም ለባለሙያዎችና ለነርሶች ዘጠኝ ያህል ሥልጠናዎችን መስጠቱንና ስድስት ስፔሻሊስት ሐኪሞች በውጭ ሀገር የስፔሻሊቲ ትምህርት እንዲከታተሉ ማድረጉን አብራርተዋል።
ማኅበሩ በቀጣይ ዓመት በአከርካሪ ሕክምና፣ በሕፃናት አጥንት ሕክምናና በከባድ ጉዳቶች አያያዝ ላይ በተለያዩ ክልሎች ሥልጠናዎችን ለመስጠት አቅዷል። በተጨማሪም በዘርፉ ያሉ ችግሮችንና የሕክምና ፍላጎቶችን በተሻለ ሁኔታ ለመለየት ሀገራዊ ምርምሮችን ለማካሄድ መታቀዱን ዶክተር ኤፍሬም ገልጸዋል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን በተዘጋጀው አውደ ርዕይ 23 የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን ይዘው ቀርበዋል። ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችም በጉባኤው በመገኘት ሥልጠና ሰጥተዋል። ከ30 በላይ የጎረቤት ሀገራት ዜጎች በኢትዮጵያ የአጥንት ሕክምና ስፔሻላይዜሽን ትምህርት እየተከታተሉ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
በጉባኤው ወቅት በዘርፉ ለረጅም ዓመታት ላገለገሉ ባለሙያዎችና በየዓመቱ ለሺዎች ለሚቆጠሩ ሕፃናት ነፃ ሕክምና ለሚሰጠው ኪዩር ኢትዮጵያ የሕፃናት ሆስፒታል እውቅና ተሰጥቷል።
የባለሙያ ፍልሰትና የሕክምና ወጪ ፈተናዎች
በአጥንት ቀዶ ሕክምና ዘርፍ እየታዩ ካሉ ዋነኛ ተግዳሮቶች መካከል የሰለጠኑ ባለሙያዎች ወደ ውጭ ሀገራት መፍለስና በተመደቡበት የሥራ ቦታ ማቆየት አለመቻል ይጠቀሳሉ። የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶች እጥረትም ሌላው ችግር ሲሆን፣ ብዙዎቹ መሣሪያዎች በሀገር ውስጥ የማይመረቱ በመሆናቸው ከውጭ ለማስገባት የሚያስፈልጉ የጉምሩክና የፈቃድ ሂደቶች መጓተት ለእጥረቱ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገልጿል።
በተጨማሪም ውድ የሆኑ የአጥንት ቀዶ ሕክምናዎች በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ሽፋን ውስጥ አለመካተታቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ታካሚዎች ለተጨማሪ ችግር እየዳረገ እንደሆነ ተነስቷል። ይህም አንዳንድ ሰዎች በዘመናዊ የሕክምና ተቋማት ፈንታ ወደ ባህላዊ የአጥንት ሕክምና እንዲያመሩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ነው።
በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሚከሰቱ የአጥንት ስብራቶችና ሌሎች ከባድ ጉዳቶች በተገቢው ሕክምና ካልታከሙ ወደ ቋሚ የአካል ጉዳትና እስከ እጅና እግር መቆረጥ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
ይህንን ለመቅረፍ ማኅበሩ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለባህላዊ የአጥንት ህክምና ባለሙያዎች (ወጌሻዎች) የምዝገባ ሥርዓት እንዲዘረጋ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ጉዳቶችን ወደ ሆስፒታል እንዲልኩ ለወጌሻዎች ሥልጠና መስጠትና የአሠራር መመሪያዎችን ማዘጋጀትም ከታቀዱት ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
Dagu Ethiopia