ከባድመ እስከ ሽራሮ፦ የትግራይ ጦርነት እና የአዲስ አበባ የፖለቲካ መልዕክቶች እዮብ ሀዲስ · 2026-11-27
አዲስ አበባ | ህዳር 18, 2019
የውጊያው መስፋፋት፣ የድሮን ጥቃቶችና የሁለቱ ወገኖች ተቃራኒ መግለጫዎች በትግራይ ያለውን የደኅንነት ሁኔታ አሳሳቢ አድርገውታል፤ በተመሳሳይ ወቅት በፓርላማ የተሰሙት የአብይ አህመድ ንግግሮች የኤርትራን ጉዳይና የውስጥ ግጭቶችን ዳግም ወደ ፖለቲካዊ መድረክ አምጥተዋል።
ከኤርትራ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙት ገምሃሎ እና ናፍራ በተባሉ አካባቢዎች ከረቡዕ እና ሐሙስ ዕለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ኃይሎች መካከል ውጊያ መካሄዱን ነዋሪዎች ተናገሩ።
የትጥቅ ግጭቶችን ቦታ እና ኹነት የሚከታተለው "አክሌድ"፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትናንት ሐሙስ ጓል ገምሃሎን እንደተቆጣጠረ እንዲሁም ይበልጥ ወደ ድንበር እየተጠጋ መሆኑን ገልጿል።
ገምሃሎ ከሽራሮ አልፎ እና ከባድመ በፊት የሚገኝ ለኤርትራ ድንበር የቀረበ አካባቢ ነው። መስከረም ላይ ተጀምሮ በፍጥነት ከዋና ዋና ከተማዎች የራቀው የትግራይ ክልል ግጭት፣ በድንበር አካባቢዎች በሚካሄዱ ውጊያዎች ቀጥሏል።
በትግራይ ሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች የተቀጣጠለው ውጊያ ከባድመ በላይ ወደ ሌሎች አዋሳኝ ቦታዎች ተስፋፍቶ መቀጠሉ ተዘግቧል። በሽራሮ፣ ገማሀሎና በአካባቢው በሚገኙ ሌሎች ስፍራዎች ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ እንደሆነ ለትግራይ መከላከያ ኃይሎች (TDF) ቅርብ የሆኑ የዲፕሎማትክ የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
ውጊያው በአየርና በምድር መቀጠሉ የተረጋጋ የሰላም ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ አዲስ የግጭት አዙሪት እየተከፈተ መሆኑን ያመለክታል።
በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መሀል ሰሞነኛው የሽራሮ ባድመ ውጊያ ኅዳር 15 ቀን 2019 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀሰቀሰ መሆኑን የሚገልጹት እነዚሁ ምንጮች፣ አሁንም እንደቀጠለ ነው። የፌዴራል መንግሥት ጦር ከሽራሮ እስከ ባድመ ባሉ አካባቢዎች ቁጥጥሩን ለማስፋፋት ዘመቻ መክፈቱን ይናገራሉ። ገምሃሎ ፣ ሸምበሊና ፣ ጓል ገምሃሎ እና ገዛ ተጋሩ በከባድ መሳሪያ ታግዞ የእግረኛ ሠራዊት በቅርብ ርቀት መግጠሙን እና በገማሀሎም የእጅ ለእጅ ውጊያ መካሄዱን ጠቅሰዋል።
የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ጀነራል መሀመድ ተሰማ ለሰራዊቱ " በ አምት ቀን ውስጥ አዲስ አበባን እንቆጣጠራለን ሲሉ ፤ መቀሌን አምስት ቀን እንዳይቆዩባት አደርገን አባረርናቸው "
ሲሉ የገለፁ ሲሆን በትግራይ ሀይል በኩል ደግሞ በኅዳር 15፣ 16 እና 17 ቀናት በተካሄዱት ውጊያዎች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን TDF በክልሉ መገናኛ ብዙሃን በኩል ገልጿል። በተለይም የፌዴራል መንግሥት ጦር በሰው ኃይልና በድሮን አቅም ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል የሚል መረጃ አቅርበዋል።
አስመራ፣ ባድመና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር
የጦር ሜዳው ውጥረት በቀጠለበት በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት ማብራሪያ የኤርትራን ጉዳይ እንደገና ወደ ፖለቲካዊ ውይይት አምጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህወሓት መሪዎች የትግራይን ውስን ሀብት በመኪና ጭነው ወደ አስመራ ገብተዋል በማለት ከከሰሱ በኋላ፣ " ወያኔ አስመራ አትገባም ተብሎ ተከልክሏል ፤ ከፈለጋችሁ ደውሉና አረጋግጡ " ሲሉ ተደምጠዋል።
ዐብይ በተጨማሪም የህወሓትን መሪዎች አሳንሰው የተናገሯቸው ሲሆን፣ በትግራይ የቀጠለውን ውጊያ በቀጥታ ከመዳሰስ ይልቅ በኤርትራ፣ በቀይ ባሕርና በውስጥ ተቃዋሚ ኃይሎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ መስጠትን መርጠዋል።
የቀይ ባሕር ጉዳይና የኤርትራ ግንኙነት
በፓርላማ ንግግራቸው ውስጥ ዐብይ ኢትዮጵያ ኤርትራን የመውረር ዓላማ እንደሌላት በድጋሚ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ሌሎችን ሀገራትን ወርራ እንደማታውቅና ወደፊትም ይህን የማድረግ ፍላጎት እንደሌላት ተናግረዋል።
ሆኖም ከኤርትራ መንግሥት ሁለት ጉዳዮችን እንደሚጠይቁ አውስተዋል። የመጀመሪያው ኤርትራ የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው የምትላቸውን ኃይሎች ማስታጠቅና መደገፍ እንድታቆም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የባሕር በርን ጨምሮ በጋራ ልማት ላይ ለመተባበር ፈቃደኛ እንድትሆን ነው።
አብይ የኤርትራ መንግሥት ይህን አቋም ካልተከተለ ውጤቱ ለኤርትራ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ማስጠንቀቂያም ተሰጥተዋል። “አድዋ ይደገማል” የሚለውንም አገላለጽ በመጠቀም ማንም ኢትዮጵያን ወሮ ያለ ጉዳት መመለስ እንደማይችል ተናግረዋል።
በአንድ በኩል የወረራ ዓላማ እንደሌለ ሲያስታውቁ፣ በሌላ በኩል ግን የኤርትራን መንግሥት በተመለከተ “ለጊዜው መንግሥት ነው” የሚል አገላለጽ መጠቀማቸው ግንኙነቱ ላይ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ይህ ንግግር የኤርትራን የፖለቲካ ሥርዓት በተመለከተ የመንግሥት አቋም ምን እንደሆነ የሚጠይቁ ትርጓሜዎችን ያስከትላል።
የውስጥ ግጭቶችና የድርድር ጥያቄ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌላ በኩል መንግሥታቸውን በትጥቅ የሚታገሉ ኃይሎችን በአንድነት የሚንቀሳቀሱ ሳይሆን እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ ናቸው በማለት ተችተዋል። መንግሥታቸው እንደማይወድቅ ገልጸው፣ በትጥቅ የሚታገሉ ኃይሎች ይህን ተገንዝበው ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ጥሪ ግን በቀጥታ የድርድር ጥሪ ሳይሆን ተቃዋሚ ኃይሎች ወዶ ገብ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ጥሪ ነው።
ወታደራዊ ሥልጠና፣ እስረኞችና የሥራ ገበያ
በፓርላማው የተነሳው ሌላው ጉዳይ የመንግሥት ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወታደራዊ ሥልጠና መውሰዳቸው ነው። ዐብይ ሥልጠናው ባለሥልጣናቱ የወታደራዊ ካምፕ ሕይወትን እንዲለማመዱ፣ መሬት ወርደው እንዲሠሩ፣ አልጋ እንዲያነጥፉ ፣ ካሊሲ ማጠብ እንዲለምዱና የዕለት ተዕለት ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ለማድረግ እንደነበር አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በመንግሥት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሠራተኛ እጥረት እንዳለ ገልጸው፣ እስረኞችን በቀን ከ500 እስከ 700 ብር እየከፈሉ እንደሚያሠሩ ተናግረዋል። በአንዳንድ የሥራ ቦታዎች እስረኞች ከድካም የተነሳ መሥራት እንደማይፈልጉ የሚገልጽ አስተያየትም ሰጥተዋል።
ይህ ንግግር በሀገሪቱ ያለውን የሥራ አጥነት ሁኔታና የሠራተኛ እጥረት ጉዳይ ሰሚን ግር አሰኝቷል። በርካታ ወጣቶች በሥራ እጦትና በደኅንነት ችግር ምክንያት ከሀገር ለመሰደድ በሚገደዱባት ኢትዮጵያ ፣ በመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ሠራተኛ መታጣቱን የቀረበው ማብራሪያ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
እስረኞች በሥራ ላይ መሰማራታቸው በፈቃዳቸው የሚከናወን መሆኑን አለመሆኑን ፣ የሥራ ሁኔታቸውን፣ የክፍያ አፈጻጸሙንና የሠራተኛ መብቶች አጠባበቅን በተመለከተ ግን ተጨማሪ ማብራሪያ የሚፈልጉ ጉዳዮች ናቸው።
የሚቀጥለው ጥያቄ፦ ጦርነት ወይስ የፖለቲካ መፍትሔ?
በትግራይ የቀጠለው ውጊያ፣ የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ የተሰሙት ንግግሮች፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያሉ የትጥቅ ትግሎች በተለያዩ ግንባሮች በአንድ ጊዜ መቀጠላቸው የኢትዮጵያን የደኅንነትና የፖለቲካ ሁኔታ የበለጠ ውስብስብ እያደረጉት ነው።
Dagu Ethiopia