ፋኖ ከ90 በላይ የጦር ሎጂስቲክስ ተሽከርካሪዎች ወደ መተማ መጓጓዛቸውን ገለጸ ዩሴፍ ምህረቱ · 2026-11-24
አዲስ አበባ | ህዳር 15, 2019
አዲስ አለም በተባለችው አካባቢ የወታደራዊ ቤዝ እየተዘጋጀ ነው ሲል የከሰሰ ሲሆን፣ የተሽከርካሪዎቹ ብዛትና ጭነት እንዲሁም የRSF ተሳትፎ በገለልተኛ ምንጮች አልተረጋገጡም።
በአማራ ክልል ጎንደር ቀጠና የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ኃይል ከ90 በላይ የጦር ሎጂስቲክስ ተሽከርካሪዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተነስተው በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ወደምትገኘው አዲስ አለም እየተጓጓዙ መሆኑን ገለጸ። ኃይሉ በኅዳር 14 ቀን 2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ተሽከርካሪዎቹ ከባድ መሣሪያዎችና የጦር አቅርቦቶችን ጭነዋል ብሏል።
መግለጫውን ያወጣው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) የጎንደር ጠቅላይ ግዛት በላይ ዘለቀ ሦስተኛ ዕዝ እንዳለው፣ ከአዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ አሶሳና ጎንደር ተነስተዋል ያላቸውን ተሽከርካሪዎች በበረራ መከታተያ መረጃዎችና በውስጥ የመረጃ ምንጮቹ ክትትል ማድረጉን ጠቅሷል። ተሽከርካሪዎቹ ወደ አዲስ አለም እየደረሱ ጭነታቸውን እያወረዱ እንደሆነም ገልጿል።
ፋኖ በተጨማሪም የአዲስ አለምን አካባቢ ወደ ወታደራዊ ቤዝነት ለመቀየር እየተሠራ ነው ሲል ከሷል። በዚህም ምክንያት ነዋሪዎች ከቀያቸው እንዲወጡ፣ ሃይማኖታዊ ተቋማት ከቦታቸው እንዲነሱና አንዳንድ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲዘጉ እየተደረገ ነውም ብሏል።
የፋኖ ኃይል ይህንን እንቅስቃሴ ከሱዳን ጦርነት ጋር በማያያዝ፣ የሱዳን ፈጣን ድጋፍ ኃይሎች (RSF) በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ወታደራዊ ድጋፍና መሠረተ ልማት እያገኙ ነው የሚል ክስ አቅርቧል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) የጦር መሣሪያዎችን በአየር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ እያስገባች እንደሆነና አቅርቦቶቹም ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተሰራጩ ነው ሲል ገልጿል።
ይሁንና ከ90 በላይ ተሽከርካሪዎች ወደ መተማ መጓጓዛቸውን፣ የጭነታቸውን ይዘት፣ የRSF ኃይሎች በአካባቢው መሰማራታቸውን ወይም አዲስ አለም በተባለው ወታደራዊ ቤዝ መቋቋሙን በገለልተኛ ምንጮች ማረጋገጥ አልተቻለም።
ዳጉ ኢትዮጵያ የተመለከተው የDNE AFRICA ዘገባ በአየር ላይ የተነሱ የሳተላይት ምስሎች በኅዳር 14 ቀን 2019 ዓ.ም በጎንደር አፄ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ላይ ትልቅ የጭነት አውሮፕላን የሚመስል ነገር እንዳሳዩ ዘገባው ያስረዳል። ይሁን እንጂ ምስሎቹ የአውሮፕላኑን ዓይነት፣ ባለቤትነት ወይም የጭነቱን ይዘት ማረጋገጥ እንደማይችሉም አስገንዝቧል። በጎንደር አዘዞ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል ጣቢያ አካባቢ የተሽከርካሪዎችና የወታደራዊ ቁሳቁሶች መኖር የሚያሳዩ ምስሎችም መታየታቸውን ጠቅሷል።
በሌላ በኩል፣ ሮይተርስ በየካቲት 2018 ዓ.ም ባወጣው ምርመራ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ለRSF ታጣቂዎች ሥልጠና የሚሰጥ ካምፕ መኖሩን ዘግቦ ነበር። የዬል ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ ጉዳዮች ምርምር ላቦራቶሪም በአሶሳ በሚገኝ የኢትዮጵያ መከላከያ ጣቢያ የጭነት እንቅስቃሴ፣ የተሽከርካሪዎች መጨመርና የግንባታ ሥራዎችን በሳተላይት ምስሎች መመልከቱን ዘግቧል። የምርምር ቡድኑ እንቅስቃሴዎቹ ከRSF ጋር ለተያያዙ ኃይሎች የሎጂስቲክስ ድጋፍ ከመስጠት ጋር የሚስማሙ እንደሆኑ ገምግሟል። እነዚህ ምርመራዎች ግን በመተማ አዲስ አለም አዲስ የRSF ካምፕ መቋቋሙን አላረጋገጡም።
የአዲስ አለም ነዋሪዎች ከቀያቸው መውጣታቸውንና የጸጥታ ስጋት መኖሩን ለአካባቢያዊ ሚዲያዎች መናገራቸው ተዘግቧል። የአካባቢው አስተዳዳሪ በበኩሉ የለቀቁት ነዋሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑንና የውጭ ታጣቂዎች መግባታቸው እንዳልተረጋገጠ መናገሩ ተጠቅሷል።
ፋኖ በመግለጫው አካባቢው የውክልና ጦርነት ማዕከል እንዳይሆንና የሀገሪቱ ሉዓላዊነት እንዳይጣስ የተለያዩ ኃይሎች በጋራ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርቧል። ኃይሉ የትጥቅ ትግሉን እንደሚቀጥልም በመግለጫው አስታውቋል።
ምንጮች፦ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ መግለጫ፣ DNE Africa፣ ሮይተርስ፣ የዬል ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ ጉዳዮች ምርምር ላቦራቶሪላቦራቶሪ።
Dagu Ethiopia