ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ ዕቃ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዲወረሱ የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ ኢክራም መሐመድ · 2026-11-16
ከ 500 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ፤ በ ሀምሌ 2018 ዓ.ም በጉምሩክ ባለስልጣን ቃሊቲ ቅርንጫፍ የተያዘ አዲስ አበባ- የገንዘብ ሚኒስቴር በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን ለመውረስና ጥብቅ ቅጣቶችን ለመጣል የሚያስችል አዲስ ረቂቅ መመሪያ አዘጋጅቷል።
የገንዘብ ሚኒስቴር በኮንትሮባንድ እቃዎችን ለማጓጓዝ የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የውርስ እርምጃ እንዲወሰድና ከባድ የገንዘብ ቅጣቶች እንዲጣሉ የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀቱን የዘገበው ካፒታል ጋዜጣ ነው።
በቀድሞው የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2014 መሠረት፣ ተሽከርካሪዎች ኮንትሮባንድ ዕቃ ይዘው ሲገኙ ባለንብረቶች በድርጊቱ ላይ ዕውቀት እንደሌላቸው በመግለጽ 100 ሺህ ብር ቅጣት ከፍለው ተሽከርካሪዎቻቸውን ያስለቅቁ እንደነበር በመረጃው ተጠቅሷል።
ይህ አሠራር ለኮንትሮባንድ ንግድ የተለመደ የሥራ ወጪ እንዲሆን በማድረግ ሕገወጥ ንግዱን እንዳበረታታና መንግሥትን ከፍተኛ ገቢ እንዳሳጣ ተገልጿል።
በሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ተግባራዊ እንዲሆን በቀረበው የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 1425/2026 መሠረት የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ፣ የጭነት መኪኖችን፣ አውቶቡሶችን፣ ሞተር ሳይክሎችን፣ ጀልባዎችን፣ አውሮፕላኖችን፣ ባቡሮችንና የጭነት እንስሳትን ይመለከታል።
ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ኮንትሮባንድ ዕቃ ከተገኘ ተሽከርካሪው ይወረሳል
በረቂቅ መመሪያው መሠረት፣ በተሽከርካሪው ላይ የተጫነው የኮንትሮባንድ ዕቃ ዋጋ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነ ወይም ከጠቅላላው ጭነት ክብደትና ዋጋ ቢያንስ 50 በመቶውን ከያዘ፣ ተሽከርካሪው እንዲወረስ ይደረጋል።
ከዚህ በተጨማሪ የኮንትሮባንድ ዕቃው ዋጋ ምንም ይሁን ምን፣ የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ተሽከርካሪው ሊወረስ ይችላል፦
- ተደጋጋሚ የኮንትሮባንድ ጥፋት ከፈፀመ፤
- ተሽከርካሪው ላይ ምስጢራዊ የዕቃ መደበቂያ ቦታዎች (ሻግ) ከተሰራለት፤
- የፍተሻ ኬላን ጥሶ ከሸሽ፤
- በጉምሩክ ባለሙያዎች ላይ ኃይል ከተጠቀመ፤
- የተሽከርካሪውን የምዝገባ ሰሌዳ ከቀየረ፤
- የጦር መሣሪያ፣ ዕፅ፣ የከበሩ ማዕድናት፣ ቅርሶችና የዱር እንስሳትን ለማጓጓዝ ሲጠቀም ከተገኘ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚፈጸሙ ጥፋቶች የቅጣት እርከን ተቀምጧል
ከባድ ሁኔታዎች በሌሉባቸውና ለመጀመሪያ ጊዜ በሚፈጸሙ ጥፋቶች ላይ በረቂቅ መመሪያው የቅጣት እርከን ተቀምጧል። ይህም፦
- የኮንትሮባንድ ዕቃው ዋጋ እስከ 100 ሺህ ብር ከሆነ፣ ከዕቃው ዋጋ ጋር እኩል የሆነ ቅጣት፤
- ከ100 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ከሆነ፣ 200 ሺህ ብር ቅጣት፤
- ከ1 ሚሊዮን እስከ 3 ሚሊዮን ብር ከሆነ፣ 300 ሺህ ብር ቅጣት እንዲጣል ያዛል።
የጭነት እንስሳት ለኮንትሮባንድ ዕቃ ማጓጓዣ ከዋሉ፣ የዕቃውን ዋጋ መቶ በመቶ ወይም የእንስሳውን አነስተኛ የገበያ ዋጋ ፤ ከሁለቱ ያነሰው ተመርጦ እንዲከፈል ይደረጋል።
የተሽከርካሪ ባለንብረቶችን የሚጠብቁ አሠራሮች
ረቂቅ መመሪያው በኮንትሮባንድ ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸውን የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ለመጠበቅ የተለያዩ ኃላፊነቶችንም አስቀምጧል።
ባለንብረቶች ዕቃ ከመጫናቸው በፊት የውል፣ የግዢ ደረሰኝና የጉምሩክ ሰነዶችን ማረጋገጥ፣ ከሾፌሮች ጋር ኮንትሮባንድ ዕቃ እንዳይጫን የጽሑፍ ስምምነት ማድረግ፣ የጂፒኤስ (GPS) መከታተያ መሣሪያ መግጠምና ተሽከርካሪዎቻቸው የተፈቀደላቸውን መስመሮች ብቻ እንዲጠቀሙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶችም የተሳፋሪዎችንና የሻንጣዎችን ዝርዝር መያዝና ተገቢውን ፍተሻ ማካሄድ አለባቸው። እነዚህን ግዴታዎች ካሟሉና አንድ ተሳፋሪ ያለባለንብረቱ ዕውቀት ኮንትሮባንድ ዕቃ ይዞ ከተገኘ፣ ተጠያቂ የሚሆነው ተሳፋሪው ብቻ እንደሚሆን መመሪያው ያመለክታል።
ባለንብረቱ በጥፋቱ ውስጥ ተሳትፎ እንደሌለው ካስረዳ፣ ነገር ግን የተጫነው ኮንትሮባንድ ዕቃ ዋጋ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በመሆኑ ተሽከርካሪው እንዲወረስ ከተወሰነ፣ በውርስ ምትክ የተሽከርካሪውን የገበያ ዋጋ 50 በመቶ እንዲከፍል ሊወሰን ይችላል።
የውሳኔ አሰጣጥና የማሳወቂያ ሂደት
የኮንትሮባንድ ጉዳዮችን የሚመለከተው ከሕግ፣ ከመረጃ፣ ከመከላከል፣ ከትራንዚትና ከዋጋ ተመን ክፍሎች በተውጣጡ አምስት አባላት የሚዋቀር ኮሚቴ ነው። ተሽከርካሪውን በቀጥታ የያዙ ባለሙያዎች በውሳኔ አሰጣጡ ላይ እንደማይሳተፉም ተጠቅሷል።
በተጨማሪም የጉምሩክ ኮሚሽኑ ተሽከርካሪው ከተያዘ በኋላ በሦስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለባለንብረቱ በጽሑፍ ማሳወቅ እንዳለበት በረቂቅ መመሪያው ተመልክቷል።
ይህ ረቂቅ መመሪያ የተዘጋጀው የጉምሩክ ኮሚሽኑ በ2018 በጀት ዓመት 738.14 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡንና ከ380 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን ተከትሎ መሆኑ የዘገበው ካፒታል ጋዜጣ ነው።
Dagu Ethiopia