በነዳጅ ዘይትና በድንጋይ ከሰል ላይ በተነሳ አለመግባባት የCOP31 ጉባኤ ያለ አጠቃላይ ስምምነት ተጠናቀቀ ተስፋዬ ወርቁ · 2026-11-23
አዲስ አበባ | ኅዳር 11፣ 2019 ዓ.ም.
የአልጄዚራና የሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ የነዳጅ አጠቃቀምን በሚመለከት በአገራቱ መካከል የተፈጠረው ከፍተኛ ልዩነት የጉባኤውን ዋነኛ ስምምነት እንዳይጸድቅ አድርጓል።
በቱርክ አንታሊያ ለሁለት ሳምንታት ያህል ሲካሄድ የሰነበተው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) በነዳጅ ዘይት፣ በተፈጥሮ ጋዝና በድንጋይ ከሰል አጠቃቀም ላይ በተነሳ አለመግባባት ያለ አጠቃላይ የፖለቲካ ስምምነት ተጠናቋል።
የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተለያዩ አገራትን በአንድ የድርድር ጠረጴዛ ላይ ያሰባሰበው ጉባኤ፣ በአስቀድሞ ከተያዘለት የመጨረሻ ጊዜ በላይ ለሁለት ቀናት ያህል ድርድሩን ቢያራዝምም ተደራዳሪዎቹን ሊያግባባ አልቻለም። በመጨረሻም የጉባኤው ፕሬዚዳንትና የቱርክ የአካባቢ ሚኒስትር ሙራት ኩሩም ረቂቅ የስምምነት ሰነዱ በሀገራቱ መካከል የጋራ ድጋፍ ባለማግኘቱ እንዳልጸደቀ አስታውቀዋል።
የአለመግባባቱ ዋነኛ ምክንያት የዓለምን የሙቀት መጠን ለመግታት የሚደረገው ጥረት የነዳጅ ዘይትን፣ የተፈጥሮ ጋዝንና የድንጋይ ከሰልን አጠቃቀም በተወሰነ ጊዜ ውስጥ በማቆም ወይም በመቀነስ ላይ መደረግ አለበት የሚለውና ይህንን ጉዳይ በስምምነቱ ውስጥ ማካተት የለበትም የሚለው አቋም መጋጨቱ ነው።
የአልጀዚራ ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ በመጀመሪያው የረቂቅ ሰነድ ውስጥ አገራት ከቅሪተ አካል ነዳጆች በመራቅ ወደ ንጹሕ የኃይል ምንጮች እንዲሸጋገሩ የሚጠይቅ ሐሳብ ተካትቶ ነበር። በኋላ በተሻሻለው ረቂቅ ላይ ግን የነዳጅ ዘይትን፣ ጋዝንና ድንጋይ ከሰልን በግልጽ የሚጠቅስ ማንኛውም አንቀጽ ከሰነዱ ተወግዷል። ከቅሪተ አካል ነዳጆች የመራቅ የጊዜ ሰሌዳን የሚመለከት ጥሪም ከረቂቁ እንደተወገደ ዘገባው ጠቅሷል።
ይህ ለውጥ በተለይ በአውሮፓ ሕብረትና በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በብርቱ በሚጎዱ የደሴት አገራት ዘንድ ተቃውሞ አስነስቷል። እነዚህ አገራት ከቅሪተ አካል ነዳጆች የመራቅ ግልጽ ቃል ኪዳን የሌለበትን ስምምነት መቀበል እንደማይችሉ አሳውቀዋል።
በሌላ በኩል የሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ አንዳንድ የነዳጅ አምራች አገራት ከቅሪተ አካል ነዳጆች ሙሉ በሙሉ የመራቅ ጉዳይ በስምምነቱ ውስጥ እንዲካተት የሚያቀርበውን ጥሪ ተቃውመዋል። ሮይተርስ በኖቬምበር 23 ባወጣው ዘገባ እንደገለጸው፣ ሳዑዲ ዓረቢያ በድርድሩ ውስጥ ተጽዕኖ የነበራት ሲሆን፣ በርካታ አገራት ከነዳጅ አጠቃቀም የመራቅ ግልጽ አቋም እንዲካተት ያቀረቡት ጥሪ በተሻሻለው ረቂቅ ውስጥ አልተካተተም።
የነዳጅ አጠቃቀምን በመቀነስ ፋንታ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀትን በቴክኖሎጂ የመያዝና የማከማቸት ዘዴ (Carbon Capture and Storage) ላይ የተሰጠውም ትኩረት በድርድሩ ውስጥ ሌላ የአለመግባባት ምንጭ ሆኗል።
የፓሪሱ ስምምነት የ1.5 ዲግሪ ግብ አደጋ ላይ ነው?
እ.ኤ.አ. በ2015 በፈረንሳይ ፓሪስ የተካሄደው 21ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ (COP21) የዓለምን አማካይ የሙቀት ጭማሪ ከቅድመ ኢንዱስትሪ ዘመን ጋር ሲነጻጸር ከ2 ዲግሪ ሴልሺየስ በታች ለማድረግና በተለይም ወደ 1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ ለመገደብ ጥረት ለማድረግ የፓሪስ ስምምነትን አጽድቋል።
ይሁንና የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስፈልገው የግሪንሃውስ ጋዞች ልቀት ቅነሳ በቂ ባለመሆኑ የዓለም የሙቀት ጭማሪ ከ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ ገደብ በላይ ሊሆን እንደሚችል የሳይንስ ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነው። የአየር ንብረት ጉዳዮች የተመድ ምንጮችም አሁን ባለው የአገራት ቃል ኪዳን መሠረት ዓለም ከዚህ ግብ በላይ የመሞቅ አደጋ እንዳለባት ያመለክታሉ።
የጉባኤው ውጤት ሙሉ በሙሉ ዜሮ አልነበረም
ምንም እንኳን ሀገራቱ በአንድ አጠቃላይ የፖለቲካ ስምምነት ላይ መድረስ ባይችሉም፣ በአንዳንድ የተለዩ የአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ መሻሻል ተመዝግቧል። ከእነዚህም መካከል በ2035 የኤሌክትሪክ ኃይል ድርሻን በመጨረሻ የኃይል ፍጆታ ውስጥ ወደ 35 በመቶ ለማድረስ የቀረበ የፈቃደኝነት ግብ በበርካታ ሀገራት ድጋፍ ማግኘቱ ይጠቀሳል። በማላመድና በአየር ንብረት ፋይናንስ ዙሪያም በተለዩ የድርድር መስኮች እድገት ተመዝግቧል።
የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤዎች ሂደት የሚቀጥል ሲሆን፣ ቀጣዩ COP32 ጉባኤ በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን ያልተጠናቀቁት ድርድሮችም በቀጣዩ ዓመት እንደሚቀጥሉ ተጠቁሟል።
በአጠቃላይ፣ የCOP31 ውጤት የአየር ንብረት ቀውስን ለመቋቋም የዓለም ሀገራት የጋራ አቋም ላይ መድረስ እየተፈታተናቸው መሆኑን ያሳያል። የሳይንስ ማስጠንቀቂያዎች እየጠነከሩ በመጡበት በዚህ ወቅት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም ልዩነቶች የጋራ የአየር ንብረት እርምጃን ማዘግየታቸው በተለይ በድርቅ፣ በጎርፍና በከፍተኛ ሙቀት ለሚጎዱ ደካማ ሀገራት አሳሳቢ ሆኗል።
Dagu Ethiopia