አሚኒስቲ በአላማጣ በሲቪል አካባቢዎች ላይ የተፈጸሙ የመድፍ ጥቃቶች እንደ ጦር ወንጀል ሊመረመሩ ይገባል አለ ቴዎድሮስ ክፍሉ · 2026-11-24
አዲስ አበባ | ህዳር 15, 2019
በኢትዮጵያ ጦርና ከእሱ ጋር በተባበረው የትግራይ ሰላም ኃይል በተፈጸሙ አራት የመድፍ ጥቃቶች 14 ሲቪሎች መገደላቸውን ድርጅቱ በራሱ ምርመራ አረጋግጧል።
አሚኒስቲ ኢንተርናሽናል በደቡባዊ ትግራይ አላማጣ ከተማ በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ከመስከረም 18 እስከ 20 ቀን 2019 ዓ.ም የተፈጸሙ የመድፍ ጥቃቶች በጦር ወንጀል ሊመረመሩ እንደሚገባ ገለጸ።
ድርጅቱ ኅዳር 14 ቀን 2019 ባወጣው ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት (ENDF) እና ከእሱ ጋር በተባበረው የትግራይ ሰላም ኃይል (TPF) በአላማጣ የሚገኙ ሰዎች በብዛት በሚኖሩባቸው ሰፈሮች ላይ በተደጋጋሚ የመድፍ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅሷል። በጥቃቶቹ 14 ሲቪሎች መገደላቸውን በራሱ ምርመራ ማረጋገጡንም አስታውቋል።
አሚኒስቲ የምርመራ ቡድኑ 28 ሰዎችን፣ ከእነሱም መካከል የጥቃቱ ሰለባዎችን፣ የዓይን እማኞችን፣ የሟቾች ቤተሰቦችን፣ የጤና ባለሙያዎችንና ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪዎችን ማነጋገሩን ገልጿል። የድርጅቱ የማስረጃ ምርመራ ክፍልም ስምንት ቪዲዮዎችን፣ 17 ፎቶግራፎችን፣ የሳተላይት ምስሎችንና ሌሎች በይፋ የሚገኙ መረጃዎችን መተንተኑን አስታውቋል።
ከተመረመሩት ጥቃቶች አንዱ በአላማጣ ቀበሌ 04 በሚገኝ የኮንዶሚኒየም አካባቢ በመስከረም 19 ማለዳ በአምስት መኖሪያ ቤቶች ላይ መድፍ በመውደቁ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ሶስት የዓይን እማኞች ለድርጅቱ መናገራቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።
ከሟቾቹ መካከል የ26 ዓመቷ ሜሮን ሰዋሰው፣ የስምንት ዓመቱ ልጇ ማርኮን ግርማህይወት እና የ33 ዓመቱ ወንድሟ ተወከል ሰዋሰው እንደሚገኙበት ገልጿል። በአጠገቡ በሚገኝ ሌላ ቤትም አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውን ሪፖርቱ አክሏል።
በሌላ ጥቃት በመስከረም 16 ቀን በአላማጣ ንጉሥ ሽሙዬ ባር አካባቢ የመድፍ ጥቃት ተፈጽሞ ቢያንስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን አንድ ጉዳት የደረሰበት ሰውና ሌላ እማኝ ለአሚኒስቲ መናገራቸው ተጠቅሷል። ጥቃቱ በመስቀል ዋዜማ ሰዎች በዓሉን ለማክበር በተሰባሰቡበት ወቅት መፈጸሙንም ሪፖርቱ ገልጿል።
ድርጅቱ በምርመራው የትግራይ ሕዝባዊ ነፃነት ግንባር (ሕወሓት) ታጣቂ ኃይሎች ግጭቱ ከመቀስቀሱ በፊት በአላማጣ በሚገኙ ሕዝብ በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎችና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ወታደራዊ መሠረቶችን አቋቁመው ነበር የሚል ግኝት ማቅረቡንም አስታውቋል።
ስድስት የተጠየቁ ሰዎች በአላማጣ የሚገኙ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከግጭቱ በፊት በሕወሓት ታጣቂዎች እንደ ወታደራዊ ማዕከል ያገለግሉ እንደነበር ለድርጅቱ መናገራቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል። አሚኒስቲ ግን በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ታጣቂዎች በጥቃቱ ወቅት ነበሩ ወይስ አልነበሩም የሚለውን በራሱ ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጿል።
የአሚኒስቲ የክልላዊ የሰብዓዊ መብት ተፅዕኖ ከፍተኛ ዳይሬክተር ያስሚን አህመድ፣ ብዙ ሰዎች በሚኖሩባቸው ሰፈሮች ላይ ሰፊ የጥፋት አቅም ያላቸውን የመድፍ መሣሪያዎች መጠቀም ለሲቪሎች ከባድ አደጋ እንደሚያስከትል ገልጸው፣ ጥቃቶቹ የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግን የሚጥሱ ሊሆኑ ስለሚችሉ እንደ ጦር ወንጀል ሊመረመሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አሚኒስቲ የሕወሓት ታጣቂዎች በሲቪል አካባቢዎች ውስጥ ወታደራዊ ቦታዎችን ማቋቋማቸው ቢረጋገጥም እንዃን ፣ ይህ ሁኔታ በመከላከያ ሠራዊቱና በአጋሮቹ ላይ ያለውን የሲቪሎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ እንደማያስቀር አስገንዝቧል።
ድርጅቱ ግኝቶቹን በጥቅምት 19 ለመከላከያ ሠራዊቱ፣ ለትግራይ የሰላም ሀይል እና ለሕወሓት በመላክ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቆ ነበር። በኅዳር 8 ደግሞ የምርመራ ውጤቱን ለመከላከያ ሠራዊቱና ለትግራይ የሰላም ሀይል አጋርቶ አስተያየታቸውን ጠይቋል። ሪፖርቱ በታተመበት ወቅት ከሁለቱ ወገኖች ምላሽ እንዳልደረሰው አሚኒስቲ ገልጿል።
ሕወሓት ግን ኅዳር 9 በላከው ባለአራት ገጽ ደብዳቤ በራሱ ላይ የቀረቡትን ክሶች በጥብቅ እንደሚቃወምና መሠረተ ቢስ እንደሆኑ ገልጿል። የትግራይ የሰላም ሀይል ቃል አቀባይም ለሮይተርስ እንደተናገረው፣ የቡድኑ ታጣቂዎች በአላማጣ ውጊያ የግንባር ተሳታፊ አልነበሩም። የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የመከላከያ ሠራዊቱና ሕወሓት ለሮይተርስ ጥያቄ ምላሽ እንዳልሰጡ ዘገባው ጠቅሷል።
አሚኒስቲ በሪፖርቱ መጨረሻ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር፣ ተጠያቂዎችን ለመለየትና ለፍትሕ ለማቅረብ ነፃ የምርመራ ሥርዓት እንዲያቋቁም ጠይቋል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ለገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች፣ ለጋዜጠኞችና ለሰብዓዊ ድርጅቶች በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን ያለ እንቅፋት መግባት እንዲችሉ ፈቃድ እንዲሰጡ አሳስቧል።
Dagu Ethiopia