ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን የሚያሰባስበው የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ ዛሬ ይጀምራል ኤሊያስ አክሊሉ · 2026-11-23
አዲስ አበባ- አምስተኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) ከዛሬ ኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን ይጠብቃል።
አምስተኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) ዛሬ ሰኞ ኅዳር 14 ቀን 2019 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 23፣ 2026) በአዲስ አበባ ይጀምራል። እስከ ኅዳር 18 ቀን ድረስ በአዲስ አበባ አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር የሚቆየው ጉባኤው፣ የአፍሪካን የጤና ደኅንነትና የራስን አቅም በራስ የማሳደግ ጉዳዮችን ዋና ትኩረቱ አድርጓል።
ጉባኤው በአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል (Africa CDC) እና በአፍሪካ ሕብረት በጋራ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ከ30 ሺህ በላይ የፖለቲካ መሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮች፣ ፈጠራ ሥራ ፈጣሪዎችና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች እንደሚሳተፉ የAfrica CDC መረጃ ያመለክታል።
የዘንድሮው ጉባኤ መሪ ሀሳብ “የአፍሪካ የጤና ደኅንነትና ሉዓላዊነት፦ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና የመቋቋም አቅም” የሚል ነው። ይህም አፍሪካ በጤና ዘርፍ ከውጭ ድጋፍ ላይ ያላትን ጥገኝነት በመቀነስ የራሷን የገንዘብ፣ የምርምር፣ የምርትና የምላሽ አቅም እንድታጠናክር በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።
እንደ Africa CDC መረጃ፣ በጉባኤው የጤና ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ ዘላቂ የጤና ፋይናንስ፣ የክትባትና የመድኃኒት ምርትን በአፍሪካ ማሳደግ፣ የወረርሽኝ ዝግጁነት፣ ዲጂታል ጤና፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የአየር ንብረት ለውጥ በሕዝብ ጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በዋናነት ይወያይባቸዋል።
ከወጪ ድጋፍ ጥገኝነት ወደ የራስ አቅም
የጉባኤው ዋና ትኩረት አፍሪካ የጤና ፍላጎቶቿን በራሷ ለመሸፈን የሚያስችሏትን ተቋማዊ፣ ሳይንሳዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሞች እንዴት ማሳደግ እንደምትችል መመርመር ነው።
አፍሪካ ከወረርሽኞችና ከሌሎች የሕዝብ ጤና አደጋዎች በተጨማሪ፣ የጤና አገልግሎት እጥረት፣ የፋይናንስ ጫናና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትሏቸውን ችግሮች እየተጋፈጠች መሆኗን Africa CDC ጠቅሷል። በዚህ ሁኔታ አገራት የራሳቸውን የጤና ፋይናንስ ምንጮች ማሳደግ፣ የመድኃኒትና የክትባት ምርትን በአህጉሪቱ ማስፋፋት፣ የምርምር ተቋማትን ማጠናከርና የጤና ባለሙያዎችን ማብቃት ከሚነሱ ዋና ጉዳዮች መካከል ናቸው።
በተለይም አፍሪካ እስከ 2040 ድረስ 60 በመቶ የሚሆነውን የክትባት ፍላጎቷን በአህጉሪቱ ለማምረት ያስቀመጠችው ዒላማ በጉባኤው ከሚነሱ አበይትተ ጉዳዮች አንዱ ነው።
ወጣቶችና ሴቶች በጤና አመራር ላይ
ከዋናው ጉባኤ በፊት ትላንት እሁድ ኅዳር 13 ቀን 2019 ዓ.ም. በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ የወጣቶች ቅድመ ጉባኤና የሴቶች በጤና አመራር ላይ ያተኮረ ጉባኤ ተካሂዷል።
በዚህ የቅድመ ዝግጅት መርሐ ግብር 4 ሺህ ወጣቶችና 200 የሴቶች አመራር ተወካዮች እንዲሳተፉ መታቀዱን Africa CDC ገልጿል። የወጣቶችንና የሴቶችን በጤና ዘርፍ ያላቸውን የአመራር ሚና ማጠናከር፣ የሥራና የሥልጠና ዕድሎችን ማስፋፋት እና በአፍሪካ የሚመነጩ የጤና መፍትሔዎችን ማበረታታት የመርሐ ግብሩ ዓላማዎች ናቸው።
የአምስቱ ቀናት የጉባኤው ዋና ዋና መርሐ ግብሮች
በዛሬው የመክፈቻ ቀን የፖለቲካ ውይይቶች፣ የአፍሪካ የእናቶች፣ የአራስ ሕፃናት፣ የሕፃናትና የወጣቶች ጤና የ2026-2030 የተግባር ፍኖተ ካርታ ማስጀመር እንዲሁም የሀገር መሪዎች ውይይቶች ተካተዋል። በተጨማሪም ከዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዋና ዳይሬክተርነት ዕጩዎች ጋር የሚካሄድ የሚኒስትሮች ውይይት በመርሐ ግብሩ ተካቷል።
ነገ ኅዳር 15 ቀን የዓለም የጤና ሥርዓት ማሻሻያ፣ የወረርሽኝ ዝግጁነት፣ የክትባት ምርትና የጤና ፋይናንስ ጉዳዮች ይወያያሉ። ከነገ ወዲያ ደግሞ የሀገር ውስጥ የጤና ፋይናንስ፣ የመድኃኒት ምርት፣ የከተሞች የጤና አገልግሎትና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላይ የሚያተኩሩ ምክክሮች ይካሄዳሉ።
በኅዳር 17 ቀን የዲጂታል ጤና፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ የመረጃ ባለቤትነትና የአየር ንብረት ለውጥ በጤና ደኅንነት ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ይመረመራል። በመጨረሻው ቀን ኅዳር 18 ደግሞ የአፍሪካ ምርምርና ፈጠራ፣ የወደፊቱ የጤና ደኅንነትና የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ላይ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ጉባኤው ይዘጋል።
የCPHIA ጉባኤ ከ2021 ጀምሮ በየዓመቱ የሚካሄድ የAfrica CDCና የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ዋና የሕዝብ ጤና መድረክ ነው። የዘንድሮው ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ የዲፕሎማሲና የተቋማት ማዕከልነቷን በሚያሳይ ሁኔታ የጤና ፖሊሲ፣ ምርምርና የአህጉራዊ ትብብር ውይይቶችን እንድታስተናግድ ዕድል ይፈጥራል።
የጉባኤው ውጤት በአፍሪካ የጤና ሥርዓቶችን በማጠናከር፣ በምርምርና በመድኃኒት ምርት ላይ የአህጉሪቱን አቅም በማሳደግ እንዲሁም የጤና አደጋዎችን በጋራ ለመከላከል የሚደረገውን ትብብር በምን ደረጃ እንደሚያሳድግ በቀጣዮቹ ቀናት የሚካሄዱት ውይይቶችና የሚወጡ ውሳኔዎች ተፅዕኗቸው የጎላ ነው።
Dagu Ethiopia